በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ የተሰራችው ሰው አልባ አውሮፕላን (drone) ከቢሾፍቱ አየር ኃይል ወደ አዳማ ከተማ የተሳካ በረራ አድርጋለች።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰው አልባ አውሮፕላንን በመጠቀም የህክምና መሣርያዎችን እና መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል ስምምነትም ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በ6 ጣቢያዎች 24 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም እስከ 5ኪ.ግ. የህክምና ቁሳቁሶችንና መድኃኒቶችን ለማድረስ የሚያስችል ነው።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስተር ጌታሁን መኩርያ (ዶ/ር ኢንጂ.) እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ናቸው።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጌታሁን መኩርያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ሰው አልባ አውሮፕላንኗ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች መሠራቷን ጠቅሰው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ መዳበር የበለጠ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሙያ ማኅበራትንና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ በቀጣይ መሰል ቴክኖሎጂዎች ሽግግር ዙርያ ከቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር