“የዳቦ ፖለቲካ!!” ― በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ

Home Forums Semonegna Stories “የዳቦ ፖለቲካ!!” ― በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10657
    Anonymous
    Inactive

    አንዳንድ ሰዎች በቅርቡ ሸዋ ዳቦ መጋገሪያ በአንድ ዳቦ ላይ 100 ፐርሰንት ዋጋ ጨምሯል ብለው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሳቢያ አብዮት ያነሳል ብለው ሲሰጉ ባየሁ ጊዜ ስቄያለሁ። የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አልገባንም ማለት ነው።

    “የዳቦ ፖለቲካ!!”
    በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ – አዲስ አበባ

    አንድ ወቅት ግብጽ ላይ የዳቦ ዋጋ 10 ሳንቲም ጨመረ ተብሎ አብዮት ተነስቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ በቅርቡም ሱዳን ላይ እንዲሁ ሆኖ ነበር።

    አንዳንድ ‘ፌስቡካውያን’ ሸዋ ዳቦ በቅርቡ በአንድ ዳቦ ላይ 100 ፐርሰንት ዋጋ ጨምሯል ብለው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሳቢያ አብዮት ያነሳል ብለው ሲሰጉ ባየሁ ጊዜ ስቄያለሁ። በዳቦ ዋጋ ጭማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይነሳል ካልን የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና አልገባንም ማለት ነው።

    ኢትዮጵያዊ ከዳቦ ዋጋ በላይም የየዕለት ኑሮውን የሚፈትን ስንት የዋጋ ንረት ጫንቃው ላይ እያናጠረበት መልካም ቀን በተስፋ የሚጠብቅ ሕዝብ እንደሆነ ለናንተ አልነግራችሁም።

    ኢትዮጵያዊ አንድ ሊትር ኬሮሲን (kerosene) ከ400 ፐርሰንት በላይ ዋጋ ጨምሮበት እንኳን ወደከሰል ምድጃው ተመልሶ እሳት እፍ ሲል እንጂ አብዮት ሲቀሰቅስ አታውቁትም።

    ኢትዮጵያዊ 5 ብር የሚገዛው ስኳር 20 ብር ሆኖበት እንኳን እንደ ድሮው ቡና በጨው ሲጠጣ እንጂ አብዮት ሲቀሰቅስ አላየነውም።

    ኢትዮጵያዊ የግል ትምህርት ቤት ክፍያ በየዓመቱ በ50 በመቶ ሲጨምርበት ልጆቹን ወደመንግስት ትምህርት ቤት ሲያዛውር እንጂ በቁጣ አብዮት ሲያነሳ አይቶት የሚያውቅ የለም።

    ኢትዮጵያዊ የትራንስፖርት ዋጋ በዓመት ስንት ጊዜ ሲጨምርበት “እንደውም ጤና ነው” ብሎ በእግሩ ሲገሰግስ እንጂ አብዮት አንስቶ ሲሯሯጥ አልታየም።

    ኢትዮጵያዊ የነዳጅ ዋጋ ከኪሱ በላይ ሲሆንበት መኪናውን አቁሞ በእግሩ ሲንከላወስ እናየው ይሆናል እንጂ “ምቾቴ ተጓደለ!” ብሎ አብዮት ሲቀሰቅስ አልታየም።

    ኢትዮጵያዊ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከእሁድ እስከ እሁድ እንዲሠራ ተደርጎ አንድ ሰዓት ቢዘገይ “አረፈድክ” ተብሎ ደሞዙ ሲቆረጥ የመጣውን በጸጋ ሲቀበል እንጂ አመጽ አቀጣጥሎ አብዮት ሲጠራ አላየንም።

    ኢትዮጵያዊ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ማግኘት ሰማይ ቤት አንደመግባት ዕድል ሆኖ እንኳን አከራዮች በየወሩ ኪራይ ሲቆልሉበት እንባውን ወደላይ ይረጭ ይሆናል እንጂ መርሮት አብዮት ሲቀሰቅስ አይተነው አናውቅም

    ኢትዮጵያዊ አንድ ኩንታል ጤፍ 3 ሺህ ብር ሲገባ “ልመደው ሆዴ” ብሎ ስንዴ ደባልቆ ሲያስፈጭ እንጂ መረረኝ ብሎ አብዮት ሲያነሳ ያየው ማንም የለም።

    ኢትዮጵያዊ ማለት ይህ ሁሉ የኑሮ መርግ ተጭኖት እንኳን ደሞዝ ስላልተጨመረለት አደባባይ ወጥቶ አብዮት ሲለኩስ የታየ ሕዝብ አይደለም።

    እናም ኢትዮጵያዊ ይህን ሁሉ ሆኖ እንኳን እንደ ቆርቆሮ የሚንኳኳ ሕዝብ ሳይሆን ሲቀጠቅጡት ቢውሉ ድምጹ ጎልቶ የማይሰማ ሕዝብ ነው።

    የሚደንቀው ነገር ሰዎች ይህ ሁሉ ፍርሃት፣ ሞኝነት፣ ባርነት የሚመስለው ሰው መብዛቱ ነው። በፍጹም!

    ኢትዮጵያዊ ስሜታዊ ሕዝብ አይደለም። “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ባይ ታጋሽ ሕዝብ ነው። “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ባይ እርጋታን ወዳድ ሕዝብ ነው። የመጣውን መንግስት ሁሉ “እንየው! ጊዜ እንስጠው! እንታገሰው” የሚል ሕዝብ ነው።

    ኢትዮጵያዊ ቁጣው እንደግስላ፣ ትዕግስቱ እንደግመል፣ የዋህነቱ እንደርግብ፣ ብልጠቱ እንደእባብ የሆነ ረቂቅ ሕዝብ ነው።

    ችግር የሚመጣው ዝምታው እንዳላዋቂነት፣ ታጋሽነቱ እንደጅልነት፣ ታዛዠነቱን እንደባርነት የተቆጠረበት ጊዜ ነው። ልብ በሉ!

    ያኔ “ከረጋ ውሃና ዝም ካለ ሰው” ብሎ መውደቂያህን ያፈጥነዋል። “መከበር በከንፈር” ብሎ የአፍህን ዋጋ ይከፍልሃል። ክብር ይፈልጋል። ንቄትን ይጠላል። ካከበርከው ያገንንሃል። ከነገርከው ይ’ረዳሃል። ካሴርክበት ድራሽህን ያጠፋዋል።

    እናም ይግባህ! በኢትዮጵያ ውስጥ ቅሬታ አብዮት ወልዶ የማታየው ለዚህ ነው። ህዝቡ ቅሬታውን ነገ ይስተካከላል በሚል ተስፋ መርሳት እና ‘እስኪ የሚሆነውን እንጠብቅ’ በሚል ትዕግስት ማመቻመች የሚችል ባህሪ ያለው ሕዝብ ነው። ዋናው ነገር ቅሬታው ተጠራቅሞ ብሶት እስኪሆን አለመጠበቅ ነው።

    በተረፈ የሕዝቡ ዛሬን በትዕግስት ማለፍን ለነገ ሃገር ዋጋ ከመስጠት ጋር እንጂ ጀርባን ለዱላ ከማመቻቸት የባርነት መንፈስ ጋር አዳብለህ አትይበት ! በትንሽ በትልቁ እንደቆርቆሮ እንዲንኳኳም አትጠብቀው። የኛ ፖለቲከኞች ትልቁ ችግር እንመራዋለን የሚሉትን ሕዝብ አለማወቃቸው ነው!

    እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው ….

    አብዮት የናፈቀው ሰው ‘አብዮት ፍሬ’ የሚባለው ትምህርት ቤት ሄዶ እጁን ይስጥ … (ቦታውን ከፈለጋችሁ እጠቁማችኋለሁ)።

    በጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሸዋ ዳቦ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.