አዲስ የተከፈተው ቆንስላ ጽ/ቤት ቆንሱል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ ቆንስላ የጽ/ቤቱ መከፈት በሚኒሶታ ግዛት ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ አባላት ምቹ ሁኔታና መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ዋሽንግተን፥ ዲሲ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግስት በሀገረ አሜሪካ በሎስ አንጀለስ ከተማ (ካሊፎርንያ ግዛት) ከሚገኘው ቆንጽላ ጽ/ቤት ቀጥሎ ሁለተኛውን ቆንጽላ ጽ/ቤት በሴይንት ፓል ከተማ (ሚኖሶታ ግዛት) ከፍቷል።
ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ የተከፈተው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት በገቡት ቃል መሠረት ነው።
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ብርቱካን አያኖ፣ የሴይንት ፓል ከተማ ከንቲባ ሚስተር ሜልቪን ካርተር፣ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ተገኝተዋል።
ክቡር አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት የቆንስላ ጽ/ቤቱ መከፈት ለአካባቢው ብሎም በመላው አሜሪካ የሚኖረውን ዳያስፖራ ለማገልግል የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል። ዳያስፖራው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚና ፖለቲካ ለውጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከምንጊዜውንም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ የተከፈተው ቆንስላ ጽ/ቤት ቆንሱል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ በበኩላቸው የጽ/ቤቱ መከፈት በሚኒሶታ ግዛት ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ የዳያስፖራ አባላት ምቹ ሁኔታና መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የሴይንት ፖል ከተማ ከንቲባ ሚስተር ማልቪን ካርተር በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤቱ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራትና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. (ማርች 2 ቀን 2019) በከተማ ደረጃ “የኢትዮጵያ ቀን” ተብሎ እንዲከበር መወሰኑንም ጠቁመዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ዋሽንግተን፥ ዲሲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦