Home › Forums › Semonegna Stories › ባህልና ቱሪዝም በኢትዮጵያ ― የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ
Tagged: ባህልና ቱሪዝም
- This topic has 1 reply, 1 voice, and was last updated 2 years, 3 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 23, 2020 at 3:55 pm #15997SemonegnaKeymaster
በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ተጀመረ
(የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ)
በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፥ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የዘንድሮውን የዋዜማ ዝግጅት በዞኑ ቸሃ ወረዳ የጠናቃ ቀበሌ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ከመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት መከበር ተጀምሯል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ታዳሚዎችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት “የመስቀል በዓል የኛነታችን መገለጫ ነው፤ የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የእርስ በእርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት ማብሰሪያ አበባ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሰው የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ማኅበረሰባችን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። አያይዘውም በበዓሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።
የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም መስቀል በጉራጌ በተለየ የአከባበር ሁኔታ ይከበራል ብለዋል – አቶ መሐመድ።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ እንደ መስቀል ያሉ ቱባ ባህሎቻችን ታሪካቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በማስወገድ የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
መርሀ-ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል አከዋወን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /UNESCO/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ባህላዊ እሴቶች (“intangible heritages of Ethiopia”) ተርታ መመዝገቡን በማስመልከት ሲሆን፥ በአከባበሩ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ትውፊቶች በትውልድ ቅብብሎሹ ውስጥ ተጠብቀው ያለ ምንም ተፅዕኖ ክዋኔዎቹ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የማስተማር ዓላማ ያለው እንደሆነ ተነግሯል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተገቢው ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ገልጸዋል።
አንድነታችን አጠናክረን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
የቸሀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፈለቀ የመስቀል በዓል በጉራጌ ሁሉም በድምቀት ከማክበር ባለፈ የጉራጌ እሴት የሚገለፅበት በመሆኑ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግበት በማስታወስ፤ በዓሉንም በድምቀት ለማክበር ሁሉም የቤተሰብ አባል የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚከበር ገልጸዋል።
ለበዓሉ ማብሰሪያ የጉራጌ ዞን የባህል ቡድንም ያሰናዳቸውን ሙዚቃዊ ክዋኔዎች እንደነ “ጊቻዌ፣ ጊቻዌ”፣ “አዳብና” የመሳሰሉት ተውኔታዊ ክዋኔዎች በሴቶችና ወንዶች የታየበት፣ የሥራ ባህልን፣ ሠርቶ ማደግን የሚያወድሱ፣ የሚያስተምሩ ማሳያዎች፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በአንድነት በአብሮነት ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት ተውኔታዊ ትዕይንቶች የተንፀባረቁበት ነበር።
September 18, 2022 at 3:02 am #51045SemonegnaKeymasterየግሸን ደብረ ከርቤ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው – አስተዳደሩ
ደሴ (ኢዜአ) – የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልን በሰላምና በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት ባህላዊና ሀይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ዋነኞቹ ናቸው።
የመስቀል/ ደመራ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ እሬቻና ፍቼ ጨምበላላን የመሳሰሉት በዓላት ደግሞ አገሪቷ ለዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ የቱርስቶችን ዓይን መማረክ የቻሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ናቸው።
በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልም ሰላሙን በማረጋገጥ ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በማክበር እስከ ዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ሥራዎች መሠራት ይገባቸዋል።።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፥ በዓሉን በሰላምና በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ናቸው።
በኮሮና ቫይረስ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚፈለገው መልኩ አለመከበሩን ጠቁመው ዘንድሮ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት በልዩ ሁኔታ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግርና በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ኮሚቴ እስከ ታች ድረስ በማዋቀር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው የመሠረተ ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮነን በበኩላቸው በዓሉን በድምቀት በማክበር አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንና የመስቀል በዓልን በግሸን ለማክበርም ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ቦታ ሁሉም ሰው ተገኝቶ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን ጥሪ አስተልፈዋል።
“ሁሉንም በዓላት ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ያሉት ኃላፊው በተለይም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የቴሌ መሠረተ ልማቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን ለማክበርም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምዕመንና ጎብኚዎች በቦታው በመገኘት ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የትራንስፖርት ችግር እንዳይከሰትም ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 22 በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመው አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉ የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።፡
ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በመሆኑ በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜአ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.