ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ

Home Forums Semonegna Stories ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪዎች በርካታ መርሀ ግብሮችን ከፈቱ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8046
    Semonegna
    Keymaster

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በዶክትሬት ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ከፍተው ተማሪዎችን ይቀበላሉ።

    ደብረ ብርሃን/ባህር ዳር – ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ (2011 ዓ.ም) የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ (bachelor degree) አራት በሁለተኛ ዲግሪ (master degree) አስራ ሁለት መርሃ ግብሮችን እንደሚከፍት አስታወቀ።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሸናፊ ለኮሙኒኬሽን ጉዳዮች እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስራ ስድስት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮችን ይከፍታል።

    ዶክተር ጌትነት አሸናፊ እንዳሉት የትምህርት ክፍሎቹ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች የመጀመሪያ ድግሪ ከ49 ወደ 53 እንዲሁም 34 የነበረውን የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ወደ 46 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

    ከተመሠረተ 11 ዓመት የሞላው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ መስኮች እያስተማረ ይገኛል።

    በተመሳሳይ ዜና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ በበሁለተኛ እና በዶክትሬት (doctorate) ዲግሪ በሚከፍታቸው 18 አዳዲስ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም አስፈላጊው ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።

    የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ተቋሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት አገራዊ እድገቱን በእውቀት ለማገዝ እየሠራ ነው።

    በተያዘው የትምህርት ዘመንም ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 12 የሁለተኛ ዲግሪና አራት የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ 250 ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ዶክተር እሰይ እንዳሉት ህግ፣ መሬት አስተዳደር፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካል ሳይንስና የመሳሰሉት የትምህርት መስኮች አዲስ የሚከፈቱባቸው ናቸው። “የተሳካ የመማር ማስተማር ተግባር ለማካሄድም ቀደም ብሎ የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉንና የመምህራን ቅጥርም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል” ብለዋል።

    የኒቨርሲቲው በአፋን ኦሮሞ ትምህርትም በዚህ ዓመት አጋማሽ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሥርአተ ትምህርት ቀረጻ ሥራ ማካሄዱንና የመምህራን ቅጥር እየፈጸመ መሆኑን ዶክተር እሰይ አስታውቀዋል።

    ተቋሙ በህክምናው ዘርፍ የተሻለ እውቅት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ “የተሻለ የማስተማርም ሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ገንብቶ የ170 መምህራንን በመቅጠር ላይ ነው” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው በመደባኛው የትምህርት መርሀግብር ብቻ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ከ8 ሺህ 700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

    በተለይም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተሻለ አቅም ያላቸውን መምህራን በመመደብ፣ ቤተ ሙከራዎችንና ቤተ መጻህፍትን በማደረጀት ጥራትን ለማምጣት እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊትም አጠቃላይ የጥራት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

    ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሮች ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል።

    ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

    ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ (ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ)

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.