አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያን (ዶ/ር ኢንጂ.) ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሮዳ ኢንጂነሪን ሠራተኞች በተገኙበት ተመርቋል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት የአርሶ አደሩን ድካም ያቃልላሉ ተብለው የተገዙ ዘመናዊ የማረሻ መሣሪያዎች ከሀገራችን ድንጋያማ መሬት ጋር ባለመስማማታቸው የሚጠበቅባቸውን ጥቅም ሳይሰጡ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ ይውላሉ። ይህ በኢትዮፕያውያን ዲዛይን ተደርጎ የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ግን ለሀገራችን መሬት ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ ነው።
ማረሻው ከተገጠመለት ሞተር ውጪ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሠራ በመሆኑ ለጥገና፣ ማሻሻያ ለማድረግና ተጨማሪ ጥቅሞችን ለመጨመር የተመቸ መሆኑን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በቀጣይ በዚሁ ባለሞተር ማረሻ ላይ አርሶ አደሩ ተቀምጦ የሚያርስበት፣ መሬቱን ለመጎልጎል የሚያስችል፣ ምርቱን ማረሻው ላይ ለመጫን የሚያስችሉ አዳዲስ ግልጋሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚዘምን የሮዳ ኢንጂነሪን ባለቤት አቶ አክሊሉ አባተ ተናግረዋል። ማጨድና መውቃት፣ እንዲሁም ምርት መሰብሰብ የሚችል መጎታችም በቀጣይ እንደሚሠራለት ተጠቁሟል። አርሶ አደሩ በቀላሉ ነዳጅ ማግኘት እንዲችል ከእፀዋት ተረፈ ምርት መሠራት የሚችል ባዮፊዩል (biofuel) እንዲጠቀምም ይደረጋል።
አርሶ አደሮቻንን እስከ ዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አላደርግናቸውም ያሉት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በቀጣይ ችግሮቻቸውን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና መፍጠር ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል። አክለውም፥ ባለሞተር ማረሻውን አርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ኖሯቸው እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።
ባለሞተር ማረሻውን ከማዘመንና ጠጨማሪ አገልግሎቶችን አንዲያረክት ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ዋጋውም ከጥንድ በሬዎች መግዣ ባነሰ ዋጋ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ጥረት ይደረጋል ተብሏል። ባለሞተር ማረሻው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በሮዳ ኢንጂነሪንግ ትብብር የተሠራ ነው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦