ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል

Home Forums Semonegna Stories ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10810
    Anonymous
    Inactive

    ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል። የብርሃኑ ነጋን ፅናትና የአቋም ሰውነቱን መካድ ነውር ነው! እሱን በፍርሃትና በአቋም የለሽነት ማማት ብልግና ነው። እሱን በዘርና በጎሳ ጉሊት መመደብ ውለታ ቢስነት ነው!

    የነጋ ቦንገር ልጅ!
    («ዘውድዓለም ታደሠ»)

    የልደቱ አያሌው ድብን ያልኩ አድናቂ ስለሆንኩና ብርሃኑ በልደቱ ጉዳይ የወሰደው አቋም አግባብነት ያለው (fair) ነው ብዬ ስለማላምን ትንሽ አዝኜበታለሁ። ሆኖም ግን እውነት እውነት ነችና ስለብሬ [ብርሃኑ ነጋ] የማልክዳቸው ሃቆች አሉ! (ስለእሱ የሰማኋቸውን “ሴራዎችን” (conspiracies) እዚህ ጋር አላነሳቸውም።)

    ብርሃኑ ነጋ እንደብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን ‘ፖለቲካ ክፍት የሥራ ቦታ ነው’ ብሎ ወደተመታው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልተቀላቀለም። በደርግ ዘመን ብዙዎች በወላጆቻቸው ሽካ ከብሔራዊ ውትድርና አምልጠው ማታ ማታ ገዳም ሰፈር ከቆነጃጅት ጋር ቡጊ ቡጊ ሲጨፍሩ ብሬ በዚያ እድሜው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሆኖ በአገሩ ጉዳይ ከሞት ጋር ሌባና ፖሊስ ይጫወት ነበር። (የሚወዳት እህቱንም አጥቷል።)

    በኢህአዴግም ግዜ ከመለስ፣ ከታምራትና ከበረከት ጋር ባለው ልዩ ወዳጅነት (special friendship) ተሞዳሙዶ ቢያሻው ስልጣን፣ ቢያሻው መሬት ሸምቶ፣ ቢያሻው ሚኒስትር፣ ቢያሻው ቀጭን ኢንቨስተር ሆኖ ዘንጦ መኖር ሲችል ላመነበት ነገር ጎምበስ ቀና ሳይል የተቃዋሚውን ጎራ ተቀላቅሏል።

    ምንም እንኳ በየትኛውም ዓለም ቢሄድ እጁን ስመው የሚቀበሉት ምርጥ ምሁር ቢሆንም ከምቾቱ ይልቅ ወደወህኒ ወርዶ ሞት ተፈርዶበታል። እስር ቤት ውስጥ የረሃብ አድማ አድርጓል። በስተርጅና ዘመኑም እንዳቅሚቲ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ተሟሙቷል። በተደጋጋሚ በርሃ ወርዷል። የፖለቲካ አኪያሄዱን ወደድነውም ጠላነውም በሚችለው አቅም ለአገሩ ህዝብ ድምፅ ሆኗል! ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው!

    ከግማሽ ምእተ-ዓመት በላይ የሃብት ማማ ላይ ከተቀመጠ ቤተሰብ ተወልዶ፣ ዩኒቨርሲቲ ደሞዙን ለምስኪን ተማሪዎች እየሰጠ አስተምሮ፣ እድሜውን ሙሉ ባለሰባት ኮከብ (seven-star) ሆቴል እንደፓፍ ዳዲ አምስት ቺኮች አቅፎ መዝናናት እየቻለ ያሻው አገር ሄዶ በዕውቀቱ ተከብሮ መሥራት እየቻለ፣ በአፍሪካ ገናና የሆነ የጦር ኃይል አለኝ የሚልን ኃይል በጦርነት አሸንፋለሁ ብሎ በወኔ የተነሳ፣ ቤተሰቡን ጥሎ በእስር የማቀቀ፣ አገሩ ላይከፍተኛ ዕውቅና እንዳለው ግለሰብ (VIP standard) መኖር ሲችል በአሸባሪነት ተፈርጆ ብላክ ሊስት (black list) ውስጥ የገባ አንድ ሰው ባፈላልግ ያገኘሁት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ብቻ ነው!

    አሁን ደግሞ ብሬ በተጋዳላይ ታርጋ የሚንቀሳቀስ ፓርቲውን አክስሞ አዲስ ፓርቲ በማቋቋም ከመጀመሪያው “ሀ” ብሎ (from the scratch) ሊነሳ ነው። ይህን ሁሉ የሚያደርገው ለምንድን ነው? ለሀብት እንዳንል እንኳን እሱ ዘር ማንዘሩም ሃብታም ነው። ለስልጣን እንዳንል ገና ድሮ በቀላሉ ማግኘት ይችል ነበር! እና ለምንድነው ህይወቱን እንዲህ በከባድ ወጥ ውረዶች የተሞላ (tragedy) ያረገው?… መልሱ ቀላል ነው። ብሬ (ብርሃኑ ነጋ) የአቋም ሰው ነው! ብሬ ላመነበት ነገር ከገገመ ገገመ ነው! አዲዮስ!

    እኔ ከላይ እንደነገርኳችሁ ‘ለብሬ እሰዋለታለሁ፣ ብርሃኑ ነጋ ያማልዳል፣…’ ምናምን የምል አድናቂው አይደለሁም። ነገር ግን አክባሪው ነኝ። ፅናትና የአቋም ሰውነቱን መካድ ነውር ነው! እሱን በፍርሃትና በአቋም የለሽነት ማማት ብልግና ነው። እሱን በዘርና በጎሳ ጉሊት መመደብ ውለታ ቢስነት ነው!

    […] የባቄላ ፍሬ የምታህል ዛኒጋባ ቤት ሳትኖርህ ቫንዳም፣ ቫንዳም መጫወት፣ የምታጣው ነገር ሳይኖር ኃላፊነት (risk) መውሰድና ከባዱን የሕይወት መንገድ መምረጥ’ኮ ያለና የነበረ ነው። ነገር ግን ሁሉ ሞልቶልህ ብርሃኑ ነጋ የመረጠውን ሕይወት ለመምረጥ የጨዋ ልጅ መሆን ይጠይቃል፣ የህሊና ሰው መሆን ይጠይቃል፣ ራስን ማክበር ይጠይቃል! ይኸው ነው!

    ረጅም ዕድሜ ለነጋ ቦንገር ልጅ!

    [ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዱአለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ መሪና ምክትል መሪ በመሆን ተመረጡ። ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 912 ድምፅ በማግኘት የፓርቲው መሪ በመሆን ተመርጠዋል። በተመሳሳይ አቶ አንዱአለም አራጌ የፓርቲው ምክትል መሪ በመሆን ተመርጠዋል። እንደዚሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ 722 ድምፅ በማግኘት ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፥ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል። — ሰሞነኛ ኢትዮጵያ]

    ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ


     

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.