Home › Forums › Semonegna Stories › ሴትየዋ በሞባይል ፈንታ ሽጉጥ ይዛ ገብታ ቢሆንስ… ቪዲዮ በመቅረጽ ፈንታ ጥይት ተኩሳ ቢሆንስ…?
Tagged: Tigist Milkesa, ሰንሰለት ድራማ, ትዕግስት ሚልኬሳ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
July 17, 2019 at 9:04 am #11433AnonymousInactive
[ ትዕግስት ሚልኬሳ እና ባሏ የማገጠባት ሴትየ በኢትዮጵያውያን ዓይን ]
ሴትየዋ በሞባይል ፈንታ ሽጉጥ ይዛ ገብታ ቢሆንስ… ቪዲዮ በመቅረጽ ፈንታ ጥይት ተኩሳ ቢሆንስ…?
(ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ)በሰንሰለት ድራማ ተዋናይዋ ትዕግስት ሚልኬሳ ጉዳይ ሙሉ ቀን ሲጻፍ የዋለውን “ትንተና” ባላውቅም የአንዳንዶችን አስተያየት ግን በአለፍ አገደም አየሁት። ብዙዎች በተለይ ሴቶች የተዋናይቷን ድርጊት “ያለ እና የሚኖር” መሆኑን እያረጋገጡ “ለቀቅ አድርጓት’ ሲሉ አይቻለሁ። በተበዳይዋ ሚስት ላይ የነገር እስክስታ የወረዱት ግን ይበዛሉ። ይህች ሴት ባሏንና አንዲት አብራው የተኛችን ሴት ድንገት ስታገኛቸው እንኳን ቪዲዮ መቅረጽ ቀርቶ አልጋ ላይ እያሉ ባገኘችው ነገር ብትገላቸው ጭምር ሕግ በጊዜው የነበረችበትን የስነ ዐዕምሮ ሁኔታ (state of mind) ከግንዛቤ በማስገባት ቅጣት ከማቅለል ነጻ እስከመልቀቅ ሊደርስ የሚችል ፍትህ ሊሰጣት እንደሚችል ግን ማወቅ ያስፈልጋል።
የተዋናይቷን (ትዕግስት ሚልኬሳ) ጉዳይ ዝርዝሩን ስለማናውቅ (ሚስት እንዳለው አታውቅም ነበር፣ በመጠጥ ሃይል ተገፋፍታ ነበር፣ ስሜት ፈትኗት ነበር፣… ምናምን የሚሉ ተገማች ግምቶችን ከግምት አስገብተን) ለጊዜው እንለፈውና….
(ስለመልካም ስነምግባር እና ለትዳር ስለምንሰጠው ከፍ ያለ ዋጋ ብለን ) ሰው እንውቀስ ከተባለ ከልጅቷ ይልቅ ከፍ ባለ መጠን መወቀስ ያለበት ልጁ ነው ብዬ አስባለሁ። አንድ ወንድ ባለትዳር ሆኖ ፣ በጋራ ቤታቸው፣ ከሚስቱ ጋር በሚተኛበት አልጋ ላይ ሌላ ሴት ይዞ ተኝቶ ከተገኘ አስቀድሞ ትዳሩን በራሱ አፍርሶታል ማለት ይቀላል። አስቀድሞ መለያየት ሲቻል አትሊስት ሚስቱን በዚህ ያህል መጠን ሞራሏን ሊጎዳው አይገባውም ነበር።
ነገሩ ከሆነ ዘንዳ እንግዲህ……
(የሕግ ባለሙያዎች’ከህሊና ዳኝነት’ ጋር ስላለው ጉዳይ እዚህ ጋ ያግዙኝና ) በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አንድ ሰው ድንገት የራስ ህሊናን መቆጣጠር በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ፣ በዚያ ተነሳሽነት ወንጀል ከፈጸመና ይህንን በበቂ ሁኔታ በማያወላዳ ማስረጃ ማረጋገጥ ከቻለ በነጻ የሚሰናበትበት ዕድል ሰፊ ነው።
ለዚህ ደግሞ ራሴ በቅርብ የማውቀው አንድ ማስረጃ ላቅርብ። (ታሪኩ “ፍቅርና ወንጀል” በሚለው ቅጽ አንድ መጽሃፌ ውስጥ የተካተተ ረጅም የፍቅር እና የወንጀል ታሪክ ነው)
አዲስ አበባ ውስጥ ሸራተን አካባቢ በአነድ ከብት ማርቢያ ግቢ ውስጥ ሁለት በስጋ የሚዛመዱ ሰራተኞች ግድግዳቸው በተያያዘ የቆርቆሮ ዛኒጋባዎች ውስጥ ይኖሩ ነበር።አንደኛው ሚስት አለችው። አንዱ ላጤ ነው። በአንድ የሃምሌ ወር ሌሊት (ቀኑ 12 ነው) ባለትዳሩ ሰውዬ ከሚስቱ ዕቅፍ ወጥቶ እንደተለመደው ላሞች ለማለብ ወደበረት ሄደ። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ዝናብ ስራ አላሰራ ሲለው ላስቲክ ራሱ ላይ ጣል ለማድረግ ፈለገና ያንኑ ለመውሰድ ተመልሶ ያልተሸጎረውን የቤቱን በር ገፋ አድርጎ ገባ። አልጋው ላይ ያየው ያልጠበቀው ትዕይንት ግን አቅሉን አሳተው። ዘመድየው ከላይ ሚስቱ ከታች “መርፌና ክር” ሆነዋል። (ከዚህ ቀደምም ይህንኑ ‘ባል ሲወጣ ውሽሜ ገባ’ አይነት ነገር የተላመዱት ይመስላል)
በዚህ የተደናገጠው ባል ‘አረ አንተ ማነህ እግዚሃርን የማትፈራ?’ አለና ምላሽ ሲያጣ ጎንበስ ብሎ ባገኘው የብረት ዱላ ሁለቱንም እዛው በተኙበት ቀጥቅጦ አስቀራቸው። ወንድየው ዘመዱ መሆኑን ያወቀው ከገደለው በኋላ ነው። ከዚያም ሄዶ እጁን ለፖሊስ ሰጠ።
አስታውሳለሁ… እኔ ስጠይቀው “የዕውነት አምላክና ቅዱስ ሚካዔል ረድተውኝ እንጂ መች እደርስባቸው ነበር” ነው ያለው።
ጉዳዩን ሲያይ የቆየው ፍርድ ቤት ባል ያልጠበቀው ክስተት በገዛ አልጋው ላይ ተከስቶ እጅ ከፍንጅ ሲገጥመው የሚሰማውን ብስጭት እና ራስን ለመቆጣጠር ያለመቻል የስሜት ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ በዚህ ቅጽበት ለፖሊስ ወደማመልከት እና ጥፋተኛን በሕግ ወደማስቀጣት ቀና ሃሳብ ሊመጣ የሚችልበት ዕድልም ቀልብም እንደማይኖረው በማሰብ ፣ ወንጀሉ በአስገዳጅ የዐዕምሮ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የፈጸመው በመሆኑ ወዘተ የሚል ትንታኔ ሰጥቶ ሰውየውን ከወራት እስር በኋላ በነጻ አሰናብቶታል።
እና ምን ለማለት ነው …
ሴትየዋ በዚያ የብስጭት ቅጽበት ውስጥ ሆና እንኳን ቪዲዮ ቀርጻ ማሰራጨት ቀርቶ ሁለቱንም ባገኘችው ነገር ‘ሲጥ’ ብታደርጋቸው ጭምር ህጉ በዚያ ቅጽበት ያላትን የህሊና ሁኔታ ከግምት በማስገባት ነጻ ሊያደርጋት ይችል እንደነበር ማሰብ ይበጃል። ያደረገችውን ብታደርግ (በጊዜው እኛም ብንሆን የሚሰማንን እና የምንሆነውን አናውቅምና) አይፈረድባትም ለማለት ያህል ነው። አንዳንዴ የብስጭት ደረጃችንን ስንገልጽ ” የማደርገውን አላውቅም ነበር” እንል የለ? እንደዚያ መሆኑ ነው።
በግሌ ሴትየዋ የነበራት የሚገርም መረጋጋት እና የጤናማ ሃሳብ ሚዛኗ ያለመዛባቱ ሁኔታ በጣም አስደንቆኛል። ወደሌላ ወንጀል እና ሃሳብ አለመግባቷም ቢያንስ ለሰዎቹም ጠቅሟቸዋል። በትንሹም በትልቁም ወንጀል ፈጽመው ‘ሰይጣን አሳሳተኝ’ ለሚሉ ሰዎች ይህች ሴት ምሳሌ ትሆናለች። ሰይጣን ሁለተኛ አጠገቧም አይደርስ ከዚህ በኋላ ! ቂቂቂቂ
(የሕግ ባለሙያዎች ትንታኔያችሁ ይጠበቃል!!)
ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.