Home › Forums › Semonegna Stories › አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አይጠናቀቅም
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 5 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 22, 2018 at 9:54 am #9023SemonegnaKeymaster
አርባ ምንጭ (ሰሞነኛ)– ከ875 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት በ2007 ዓ.ም. በ6 ሄክታር መሬት የግንባታ ሥራው የተጀመረውና በ2 ዓመት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በአገራዊ የገንዘብ ግሽበትና የእቃዎች ዋጋ መናር ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገለጸ።
የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድኅን እንደገለጹት ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከጠየቀው 450 ሚሊየን ብር በጀት በፌዴራል መንግሥት የተፈቀደው 166 ሚሊየን ብር ብቻ ሲሆን ይህም ገንዘብ ቢሆን በወቅቱ ሊለቀቅ አልቻለም። የበጀት ችግሩ እንዳለ ሆኖ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር መግባባት በመፍጠር በተቻለ መጠን ሥራዎች አየተሠሩ መሆኑን ተወካይዋ ተናግረዋል።
ከአገር አቀፍ የገንዘብ እጥረቱ በተጨማሪ የዲዛይን ሥራዎች እና በሆስፒታሉ ዙሪያ የድንበር ማካለሉ ሥራ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቅ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ ካደረጉ ምክንያቶች ዋናዎቹ ናቸው። ድንበር ማካለሉን አስመልክቶ በሆስፒታሉ ዙሪያ ከይዞታቸው ተነሺ ከሆኑ 60 መኖሪያ ቤቶች ለ47ቱ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጋር በመሆን ተመጣጣኝ ተለዋጭ የመኖሪያ ቦታ ተመርጦ የዲዛይኑ ሥራ ያለቀ ሲሆን በዩኒቨርሲቲውና በከተማው ማዘጋጃ ቤት ትብብር ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን በሂደት ላይ ነው። ለቀሪዎቹ ተነሺ ነዋሪዎችም ለመኖሪያ ቤት የሚሆን የቦታ መረጣ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
◌ ተመሳሳይ ዜና፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ዘመንዊ የህክምና ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎችች ባለስልጣናት በተገኙበት ተመረቀ
የሆስፒታሉን ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘው ይርጋለም ኃ/የተ/የግል ማኅበር መሀንዲስ ይህደጎ ተስፋዬ እንደተናገሩት የግንባታ ሥራዎች በታቀደላቸው ጥራት በመከናወን ላይ ቢገኙም በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚለቀቀው ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ አለመድረስ፣ በአማካሪው በኩል የዲዛይን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አለማለቅ እንዲሁም የድንበር ወሰን ማካለል ችግር ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳይጠናቀቅ ምክንያቶች ሆነዋል። የጋዝና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሲስተሞቹ በሪፈራል ሆስፒታል ግንባታዎች ከተሰማራንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ዘመናዊነትን የተላበሱ ናቸው ያሉት መሀንዲሱ፥ በአጠቃላይ ሊገነቡ ከታሰቡት 11 ግንባታዎች የሪፈራል ሆስፒታሉ ዋና ህንፃ፣ የአካል ጉዳተኞች መወጣጫ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ብቻ ግንባታቸው ከ90% በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ 7 የመወጣጫ ሊፍትና 400 አልጋዎች ያሉት ዘመናዊው ሆስፒታል በውስጡ መረጃዎች በዘመናዊ መልክ የሚደራጁበት ዳታ ሲስተም (Data System)፣ ህመምተኞች በቀላሉ የህክምና ባለሙያዎችን የሚጠሩበት ነርስ ኮል ሲስተም (Nurse Call System)፣ የሆስፒታሉን ደኅንነት የሚቆጣጠሩ ዲጂታል ካሜራ ሲስተም (Digital Camera System)፣ ታካሚዎችን የሚያዝናኑና በቂ መረጃን የሚሰጡ የቴሌቪዥን ሲስተም (TV System) እና መሰል ዘመናዊ ሲስተሞች የተገጠሙለት ነው።
የዘመናዊውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የማማከር ሥራ የሚሠራለት ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለመማር-ማስተማር ሂደት አጋዥ ከመሆኑም በተጨማሪ ለምርምር ሥራ መዳረሻ እንደሚሆን ይሆናል።
ምንጭ፦ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 15, 2019 at 6:45 am #9708AnonymousInactiveየትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም (ትእምት) ለመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል 11 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
—–የትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም የበጎ አድራጎት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታረቀ የገንዘብ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ ሆስፒታሉ የተሻለና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማጠናከር በማሰብ ነው።
የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ዓመታት ከአፋር፣ አማራና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ ህሙማን ጭምር አገልግሎት መስጠቱን አስታውሰው፣ ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት እንጻር ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ሳይሟሉለት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የህሙማን ህክምናና እንክብካቤ የሥራ ሂደት ተጠባባቂ አስተባባሪ አቶ በሪሁ መስፍን የገንዘብ ድጋፉ ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና መሳሪያዎች ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሚፈታ ተናግረዋል።
የገንዘብ አርዳታው በሆስፒታሉ የሚገኙትን ያረጁ የህክምና መሳሪያዎች፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎችና ኬሚካሎችን እጥረት በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይብራህ አለማየሁ ናቸው።
የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል በዓመት ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን እስከ 5 ሺህ ነፍሰጡር እናቶችንም እንደሚያዋልድ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.