አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ ዙር የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

Home Forums Semonegna Stories አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ ዙር የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #8845
    Semonegna
    Keymaster

    አርባ ምንጭ (አ.ም.ዩ.)– አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 76 የህክምና ዶክተሮች ኅዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በደማቅ ሥነ ስርዓት አስመርቋል።

    የዩኒርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት መርሀ ግብሮችን (ፕሮግራሞች)እና የሚካሄዱ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

    ዩኒቨርሲቲው የጤና ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ፥ የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 127 መምህራን እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን 69ኙ 2ኛ ዲግሪ፣ 11ዱ 3ኛ ዲግሪ እና 41ዱ የስፔሻሊቲ መ/ራን ደረጃቸውን ሊያሻሽል ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

    እንደ ፕሬዝደንቱ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ሆስፒታልና አጎራባች የጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር፣ በማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ምርምሮችን በማከናወንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው።

    Selale University (Fiche, Ethiopia) accepts students for the first time

    ፕሬዝደንቱ በህክምና ትምህርት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በተመለከተ በ2009 ዓ.ም. ከነበሩት 58 የህክምና ዶክትሬት ምሩቃን መካከል የሴት ምሩቃን ቁጥር 1 (አንድ) ብቻ የነበረ ሲሆን በ2011 ዓ.ም. ከተመረቁት 76 የህክምና ዶክተሮች የሴት ምሩቃን ቁጥር 18 መድረሱ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በተጨማሪም ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከሥራው ዓለም ጋር አዋህደው የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ለአገራችን ህዳሴ ታላቅ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በድሩ ሂሪጎ በበኩላቸው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ የወባ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም መሰል የጤና መሻሻል ሊያመጡ የሚችሉ አገር አቀፍ ምርምሮችን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን እየተገነባ ያለው የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ጥራት ያለው የጤና ትምህርትና የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ያስችላል።

    ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በአገራችን ትምህርትና ሥልጠና አቅርቦት፣ ተገቢነትና ጥራት ላይ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ያለነው በታዳጊና ኢኮኖሚዋ ባልዳበረ አገር እንደመሆኑ መጠን ምሩቃን ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በመጋፈጥ በድል መወጣት፣ ቀና አስቢነትንና ትህትናን መላበስ እንዲሁም በአሸናፊነት እና በ”እችላለሁ!” ስሜት ተነሳሽነት የወገናችውን ህይወት የሚቀይር ሃሳብና አሠራር ሊቀይሱ ይገባል በማለት አሳስበን ንግግራቸውን በመቀጠል፦

    ‹‹ዛሬ ተንብዩ፤ ለነጋችሁ ያለእረፍት ሥሩ፤ የምትይዙት ጓደኛ፣ የምታዩት ፊልም ሁሉ ከህልማችሁ እና መድረሻችሁ ጋር የተገናኘና ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያግዛችሁ መሆኑን አረጋግጡ›› ያሉት ሚኒስትሯ ዘረኝነት፣ ሌብነት እና ራስ ወዳድነት ከአገራችን ወግና ባህል የወጡ በመሆኑ ልትታገሏቸው ይገባል ብለዋል ።

    የኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር ተወካይ እንዲሁም የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ዶ/ር መስከረም አለቃ በበኩላቸው የተመረቃችሁበት ሙያ ትልቁን የሰው ልጅ የማዳን ተግባር በመሆኑ በሥራው ዓለም የሚጠብቋችሁን ተግዳሮቶች በትጋት በመወጣት ለወገናችሁን ጤና መሻሻል ልትሠሩ ይገባል በማለት ለአገሪቱ ጤና መሻሻል በጋራ ለመሥራት ለምሩቃኑ በማኅበሩ ሥም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ እንዳስደሰተው የገለፀውና 3.54 አማካኝ ወጤት በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ የሆነው ምሩቅ መሠረት ሙሉ በቀጣይ የማህፀንና ፅንስ ሐኪም መሆን እንደሚፈልግና የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠብቀው ተናግሯል።

    አማካኝ ወጤት 3.46 የማዕረግ ውጤት በማምጣት ሴቶች በህክምና ትምህርት ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ መኖሩን ጥሩ ማሳያ የሆነችው ምሩቅ ትዕግስት ገረሱ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ሊቀንሱ የሚችሉ በቂ ምርምሮችን በማከናወን ባለት ዕውቀትና ክህሎት ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነች ገልፃለች።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.