ከህመሜ እስከ ስደቴ አብሮኝ ለታመመውና በመንፈስ አብሮኝ ለተሰደደው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን – የባህል ሙዚቃ አቀንቃኙ አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በባሕር ዳር ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ላደረጉለት ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ
ባሕር ዳር (አብመድ)– ላለፉት ስድስት ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገውና የባህል ሙዚቃ አቀንቃኙ አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ባሕር ዳር ገብቷል። በባሕር ዳር ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም አድናቂዎቹ አቀባበል አድርገውለታል።
የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከፍተኛ እና ያመነበትን የሚያቀነቅን እንደሆነ የሚነገርለት አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ነው። “ነፃነት በተነፈገው ህዝብ መካከል በኖርኩባቸው ዓመታት ከህመሜ እስከ ስደቴ አብሮኝ ለታመመውና በመንፈስ አብሮኝ ለተሰደደው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለመገናኘት አበቃን” ያለው አርቲስት ፋሲል ከዚህ ጋር አያይዞም “መድረክ ላይ እንዳልዘፍን የተከለከልኳቸውን የሙዚቃ ስራዎቸን በዚህ ህዝብ ፊት ለማቅረብ በመታደሌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
በቀጣይ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሰህ ህዝብን የማግኘት ዕድል እንደሚኖረው በአቀባበሉ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች ላቀረቡለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ አርቲስቱ ከአሜሪካን ሀገር ወደ አገር ቤት ያመጡኝ አስተዋዋቂዎች (ፕሮሞተሮች) የሚያውቁት ሆኖ እስካሁን ባለኝ መረጃ በባሕር ዳር ከተማ አንድ የሙዚቃ ድግስ መኖሩን ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
“ድግስ ጠርቻችኋለሁ” ያለው አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ስለታገላችሁለት ነፃነት በነፃነት እንጫዎታለን ነው ያለው። በአርቲስቱ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላያ የተገኙት እማሆይ ፀሃይ ዓለሙ “ፋሲልን በስራዎቹ እና በሀገር ፍቅሩ እወደዋለሁ” መጣ ሲባል ስለሰማሁ እንኳን ለሀገርህ አበቃህ ለማለት ነው የመጣሁት በማለት ለየአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች መልስ ሰጥቷዋል።
በተመሳሳይ የቀድሞ ጓደኛው እና የሥራ ባልደረባው አርቲስት ቹቹ ምስጋናው ለፋሲል ያለው ፍቅር እና አክብሮት የተለየ መሆኑን ገልፆ “ለኢትዮጵያ ገና በርካታ ሥራዎችን የሚሠራ እና አሉ ከሚባሉ የባህል ሙዚቀኞች አንዱ በመሆኑ እንኳን ወደ ሀገሩ በሰላም ገባ” ሲል በአርቲስቱ መምጣት የተሰማውን ደስታ ገልጻል።
የአርቲስት ፋሲል ደመወዝ እህት እስከዳር ደመወዝ በወንድሟ ወደ ሀገር መመለስ የተሰማት ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻ በህመሙ እና በስደቱ ወቅት ከጎኑ ለነበረው ህዝብ ምስጋናዋን አቅርባለች።
አርቲስት ፋሲል ደመወዝ በባሕር ዳር ስታዲየም ህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም “ሀገሬ ኮንሰርት” በሚል መሪ ሃሳብ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለህዝብ ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል ሲል የዘገበው አብመድ ነው።
አርቲስት ፋሲል ደመወዝ ወደ አሜሪኣ ከተሰደደ በኋላም የሙዚቃ ሥራውን አድናቂዎቹ ያቀርብ የነበረ ሲሆን የተለያዩ ነጠላ ሙዚቃዎችን፣ እንዲሁም አማርኛ ሙዚቃ አድማጭ ዘንድ እጅግ ተቀባይነት ያገኘለትን “እንቆቅልሽ” የተሰኘ አልበም ሠርቷል። በአሜሪካ እና በካናዳ የተለያዩ ግዛቶችም እየተዘዋወረ የሙዚቃ ዝግጅቶች (ኮንሰርቶች) ላይ ከአድናቂዎቹ ጋር ተገናኝቷል። አሜሪካ ውስጥ ፍሎሪዳ ግዛት ካቀረበው ኮንሰርት ላይ የተቀነጨበውን እዚህ ጋር ይመልከቱ።
ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ)