Home › Forums › Semonegna Stories › አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ደመቀ መኮንን በድጋሚ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 3 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 5, 2018 at 12:31 pm #7891SemonegnaKeymaster
በተደረገው ምርጫ በጠቅላላው 177 ሰዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ዶ/ር አብይ አህመድ 176 ድምጽ በማግኘት የሊቀ መንበርነቱን ሹመት ሲያገኙ አቶ ደመቀ መኮንን ደግም 149 ድምጽ አግኝተው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ሀዋሳ (ኢዜአ/ፋና)፦ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሲካሔድ የነበረው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ሰባት የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት አርብ መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ በጉባዔው ማጠቃለያም ዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮንን በድጋሚ የግንባሩ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
በምስጢር በተደረገው ምርጫ በጠቅላላው 177 ሰዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ዶ/ር አብይ አህመድ 176 ድምጽ በማግኘት የሊቀ መንበርነቱን ሹመት ሲያገኙ አቶ ደመቀ መኮንን ደግም 149 ድምጽ አግኝተው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ዶ/ር አብይ አህመድ (በግራ) እና አቶ ደመቀ መኮንን (በቀኝ)
ግንባሩ ባወጣው የማጠቃለያ መግለጫ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ጠንካራ የአስተሳሰብ አንድነት በመያዝ ከአሰራር፣ ከአደረጃጀትና ከአመራር ግንባታ አንጻር ያሉበትን ጉድለቶች ፈትሾ በማስተካከል እንዲሁም ጥናት ላይ በመመሥረት የርዕዮተ ዓለም ማልማትና ማሻሻል ሥራን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለውጡን በሚፈለገው ፍጥነት መርተን ከግብ ለማድረስ በጋራ እንደሚሠራ ሲል በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የዴሞክራሲ ምህዳሩን የበለጠ ማስፋት፣ ዜጎች በያዙት የተለየ የፖለቲካ ሀሳብና አመለካከት የማይገፉበትና በጠላትነት የማይታዩበት ሀገራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር የግልና የቡድን መብቶች በተሟላ መልኩ የሚከበሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድ በፅናት እንደሚታገሉ መግለጫው አትቷል፡፡
የማንነትም ይሁን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የሚመለከታቸውን ሕዝቦች ነጻ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕገ-መንግሰታዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲፈቱ፣ የዜጎች የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት የመኖር፣ በቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት፣ ወግና ባህላቸውን የማሳደግ፣ ተገቢውን እውቅናና ውክልና የማግኘት፣ ሃብት የማፍራት ሕገ-መንግሰታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ ብሔራዊ ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሳይነጣጠሉ እንዲከበሩ በትኩረት እነደሚሠራም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
በገጠርም ሆነ በከተማ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን የሚያጠናክሩ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚያስችሉ የመላውን ህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን የሚያደርግ በተለይም የወጣቶችና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ቃል ገብቷል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት አንድነትና መልካም ጉርብትናን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራም በመግለጫው ተመልክቷል።
ሀገራችን ሰላም የሰፈነባት፣ ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ያለስጋት የሚኖሩባት የህግ የበላይነት የተከበረባት፣ ነጻነት ከህግ የበላይነት ውጭ ባርነት መሆኑን በመገንዘብ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታን ጠንቅቆ የሚያውቅ ህብረተሰብ ለመገንባት በትጋት እንደሚሠራ በመግለጫው ተጠቁሟል።ድርጅታችንን የማጠናከር ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ህዝቡን ለመካስ ቃል ገብቷል።
ምንጭ፦ ኢዜአ/ፋና
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.