አዲስ የተሾሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?

Home Forums Semonegna Stories አዲስ የተሾሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #11466
    Anonymous
    Inactive

    ባህር ዳር (አብመድ)፦ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው የጸደቀላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክር ቤት አባላትና ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    እንደ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንትነት ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ንግግር ያደረጉት አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ እንዲመለሱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

    በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለኢንቨስትመንት ዕድገትም አትኩሮት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስከትለውም “የሕግ የበላይነትን ማስፈንም ለነገ የምንለው ጉዳይ አይሆንም” ብለዋል ለአማራ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት።

    ለመሆኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል።

    በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (University of Greenwich) በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።

    ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በፌደራል መንግስት ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

    በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል።

    ፌደራል መንግስት ደረጃ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል።

    አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል።

    የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

    ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አቶ ተመስገን ጥሩነህ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.