Home › Forums › Semonegna Stories › ውጤታማ የማኅበረሰብ-አቀፍ የአኩሪ አተር የመነሻ ዘር ብዜት ሥራዎች በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 26, 2018 at 5:48 am #8252SemonegnaKeymaster
ፓዌ ወረዳ (የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) – መገኛው ከምስራቅ እስያ እንደሆነ የሚነገርለት አኩሪ አተር አሜሪካንና ቻይናን ጨምሮ በርካታ የአለም አገራት በስፋት በማምረት ለምግብነት ማዋል ከጀመሩ ሁለት ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል። አኩሪ አተር ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን በውስጣቸው ከያዙ የሰብል ዓይነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሲሆን የቪታሚን፣ የማዕድንና ሌሎችም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑ በሰው ልጅ የአመጋገብ ስርዓት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል።
በሰብሉ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነም የልብ ህመም፣ የደም ግፊትና ካንሰርን ጨምሮ ለበርካታ የሰውን ልጅ ሊያጠቁ የሚችሉ የበሽታ አይነቶች መፍትሄም ነው። በዚህም አኩሪ አተር በአጭር ጊዜ ውስጥ በ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነትን ሊያገኝ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም አኩሪ አተር በውስጡ የያዘው የዘይት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ ኢንዱስትሪዎች እየታየ ያለው የምርት ፍላጎት ከፍተኛ ሲሆን የአፈር ለምነትን ለማሻሻል የሚረዳ የሰብል ዓይነት ነው። ለእንሰሳት መኖነትም በከፍተኛ ሁኔታ ይውላል።
አገራችን ኢትዮጵያም አኩሪ አተርን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የተስማሚነት ጥናት በማካሄድ፣ በማላመድና በማምረት ለምግብነት ማዋል ከጀመሩ አገራት ውስጥ አንዷ ናት። አኩሪ አተር ወደኢትዮጵያ ገብቶ መመረት ከጀመረ አራት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እንደሆነ ይነገራል። በሰብሉ ዙሪያ በተደረጉ ምርምሮችም ከ25 በላይ ቴክኖሎጂዎች ማውጣት ተችሏል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወጡ ናቸው። አገራችን አኩሪ አተርን በስፋት ለማምረት አመቺ የሆነ ሰፊ መሬትና አየር ንብረት ያላት ከመሆኑ ገር በተያያዘ በርካታ አገራት ያሳዩት የንግድ ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም በዚሁ ሰብል እተሸ ፈነ ያለው መሬት ስንመለከት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፉ ላሉ የምግብ ዘይትና የእንሰሳት መኖ አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት ፍላጎት የሚመጥን ምርት ማቅረብ አልተቻለም።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል) ከአኩሪ አተር ሰብል የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ለረጅም ጊዜያት ምርምር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን የዝናብ መጠናቸው ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች ተስማሚ እንዲሁም በሽታንና ተባይን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ የአኩሪ አተር ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙ የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ውጤታማና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት እንዲቻል የአመራረት ሂደትን የተከተሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ቪድዮ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማሮ ወረዳ በቡላ ምርት ላይ የተሠማሩ ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ስለማይደረግላቸው እየተዳከሙ ነው
ማዕከሉ በዚሀ ዓመትም በመተከል ዞን በፓዌና ማንዱራ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን በማቀናጀት የማኅበረሰብ አቀፍ የአኩሪ አተር ቴክኖሎጂ መነሻ ዘር ብዜት ሥራዎችን አከናውኗል። ይህንንም ተሞክሮ በማስፋት ሌሎችም የአካባቢው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ለማመቻቸትና ፍላጎት ለመፍጠር የሚረዳ አርሶ አደር የመስከ ቀን ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም አካሂዷል። በዚሁ በዓል ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንዳንድ የአካባቢው አርሶ አደሮች እንደገለፁትም ሰብሉን ማምረት እያስገኘ ያለውን ጠቀሜታ ከሌሎች አርሶ አደሮች በመረዳታቸው የአኩሪ አተርን ለማምረት ፍላጎት ያደረባቸው ቢሆንም የመነሻ ዘር አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል። ለዚህም ችግር መፍትሄ እንደሚያገኙ በመተማመን ወደ ምርምር ማዕከሉ እንደመጡ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሁለተኛው የግብርና እድገት ፕሮግራም አሰተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ሶፊያ ካሳ በዚሁ የአርሶ አደር መስክ ቀን መርሃ ግብር ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት በአኩሪ አተር ዙሪያ የተከናወኑ የማስተዋወቅና የማስፋፋት እንዲሁም ዘር ብዜት ስራዎች የኢንስቲተዩቱ ቴክኖሎጂዎች ያላቸው ተደራሽነተት ምን ያህል ነው የሚለውን ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን በአገሪቱ ለረጅም ጊዜያት ሲነሳ የቆየውን የመስራችና ቅድመ መስራች ዘር አቅርቦት እጥረት ችግር ኢንስቲትዩቱ በተያዘው በጀት ዓመት ከክልል ግብርና ምርምር ተቋማትና ከሌሎችም አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት አርሶ አደሩe በማደራጀትና ስልጠና እንዲያገኝ በማድረግ የመስራችና ቅድመ መስራች ዘር ብዜት ሥራን በጥራት የማከናወን ተግባር እያከናወነ እንደገኝ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና አካባቢው አኩሪ አተርን ጨምሮ ለበርካታ ሰብል ምርት አመቺ የሆነ አካባቢ በመሆኑ በተመሳሳይ የሚታየውን የመነሻ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ከአካባቢው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ጋር ያለውን ትስስር በማሳደግ የሰብል ምርትን አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ መስራት ይኖርበታል ሲሉ ይገልፃሉ። ዶ/ር ሶፊያ አያይዘውም አርሶ አደሩ መስኖን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት የሚያስችለው አቅም ላይ እንዲደርስ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
የአኩሪ አተር ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ ዘንድ በስፋት እንዲደርስ ለማድረግም የማስተዋወቅና የማስፋት ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ መሠራት የሚኖርባቸው ሲሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ በማሳደግም በክላስተር እንዲደራጁ በማድረግ በባለሞያዎች እገዛም ጥራቱን የጠበቀ የመነሻ ዘር ብዜት በማከናወን በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካባቢውን አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚቻል መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቅድመ-መስራችና መስራች ዘር አቅርቦት ሃላፊነት የምርምር ተቋማት ቢሆንም የአገሪቱ የምርምር ተቋማት ካላቸው የአቅም ውስንነት መነሻነት መነሻ ዘሮችን በስፋት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ አይቻላቸውም። በመሆኑም የዘር ብዜት ስራን በሃላፊነት ከሚያከናውኑ ተቋማት በተጨማሪም አርሶ አደሮችን በማደራጀትና ተገቢውን የሰብል አያያዝ ስልጠና በመስጠትና ክትትል በማድረግ ምርትን ማስፋት ከማስቻሉም ባለፈ መነሻ ዘር ላይ የሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችን በመቅረፍ የሰብል ምርቶችን በስፋት ለኢንዱስትሪ ግብአትነትና ለውጭ ንግድ ማዋል የሚያስችል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ይሆናል።
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ፓዌ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ ምርምር ማዕከሉ በሰብል በእንሰሳትና ተፈጥሮ ሃብት የምርምር ዘርፎች ለረጅም ጊዜያት የምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም በርካታ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማላመድ፣ በማስተዋወቅና የማስፋት ሥራዎችን በማከናወን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል፤ እየሰራም ይገኛል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.