Home › Forums › Semonegna Stories › የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት በተጠና ዕቅድ ያልተመራ እንደነበር ተገለፀ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 9 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 19, 2019 at 10:04 pm #9800SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን የግንባታ አፈፃፀም በፌዴራል ዋና ኦዲተር የተደረገ የክዋኔ ኦዲት መሠረት በማድረግ ይፋዊ ስብሳባ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. አካሂዷል። በስብሰባው ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት በተጠና ዕቅድ ላይ ያልተመራ እንደነበረ ገልጿል።
በኦዲት ሪፖርቱ ግንባታዎቹ በምዕራፍ ተከፋፍለው መቼ እንደሚሠሩ፣ እያንዳንዱ ሥራ ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅና በአጠቃላይ በመሪ ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ ባለመደረጉ በግንባታው ሊሟሉ የሚገቡ የግብዓት፣ የቤተ ሙከራና የመፅሐፍት ግዥ ማሟላት እና የካሣ ክፍያ በተገቢው ሁኔታ መፈፀም አለመቻሉ ተገልጿል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ11 ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደስታ በሰጡት ምላሽ ግንባታዎቹ የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ ቢያዘጋጁም በዕቅዱ መሠረት ለማከናወን የበጀት እጥረት በመኖሩ በዕቅዱ መሠረት መፈፀም እንዳልተቻለ፤ የግብዓትና የቤተ ሙከራ እቃዎችን የመንግሰት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በወቅቱ ባለማቅረቡ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ገልፀው፥ እንደመፍትሔ ተማሪዎች ወደ አጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው የቤተ ሙከራ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ እንደሚገኝ እና የካሣ ክፍያን በተመለከተ ክልሎች የተከፋዮችን ዝርዝር በተሟላ ሁኔታ አደራጅተው የማይልኩና ለተከፋዮቹም በቀጥታ በአካውንታቸው እንዳይገባ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ ክፍያው እነሱ በፈለጉት አግባብ መፈፀሙን ተናግረዋል።
◌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ማሰገንቢያ የሚውል አስር ሚሊዮን ብር ለገሰ
ለዲዛይን መጣጣምና ቁጥጥር ለሚሠሩ አማካሪዎች ክፍያ በበጀት ብር 28,600,000.00 የተያዘ ሲሆን ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር ውል ሲፈራረሙ ብር 117,668,636.09 በመሆኑ ብር 89,068,636.09 (311%) በብልጫ መዋዋሉ የኦዲት ግኝቱ አመልክቷል።
አማካሪዎች ክፍያን በተመለከተ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ምላሽ 28 ሚሊዮን ብር በ2008 ዓ.ም. /ለአንድ ዓመት/ ብቻ ለሚከናወን ግንባታ የተገመተ እንደሆነ እና ብር 117 ሚሊዮን ግንባታው በሚቆይባቸው አጠቃላይ ዓመታት የተቀመጠ ወጪ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሠራቸው የግንባታ ሥራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የሚጠበቅበት ቢሆንም ቅንጅት ባለመፈጠሩ ምክንያት የውሃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ችግር ማጋጠሙን፣ የካሣ ክፍያ ተፈፅሞላቸው ከይዞታቸው ያልተነሱ መገኘታቸውን እና በደምቢ ዶሎ፣ በወራቤ፣ በራያ፣ በመቅደላ፣ በአምቦና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ለካሣ ክፍያ በበጀት ለግንባታ ተነሽዎች 100 ሚሊዮን ተይዞ የነበረ ቢሆንም ተከፍሎ የተገኘው 215,071,377.16 መሆኑንና ይህም ክፍያ የብር 115,071,377.16 ብልጫ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ከመፍጠር አንጻርም ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር በተለያየ ሁኔታ እንደተደረገላቸው፤ የሚመለከታቸውን አካላትን ማወያየታቸውንና አስፈላጊ ክፍያዎችንም ለአገልግሎት አቅራቢ ተቋማት መፈፀማቸውን ገልፀው ነገር ግን በተለይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስካሁን በተሟላ ሁኔታ ሊያገኙ አለመቻላቸውን የተቋሙ ኃለፊዎች ተናግረዋል።
◌ በኦሮሚያ ክልል አቦካዶ አምራች ገበሬዎች የተሻሻሉ ዘሮችን በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደግ ችለዋል
በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የ3,210,218.24 ብር የካሣ ክፍያ ሰነድ ማስረጃ ሳይኖረው መከፈሉን፤ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ሳይት 17 አባወራዎች የግንባታ ካሣ ቢከፈላቸውም አለመነሳታቸው፤ በራያ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጀክት ለሚገኙ 35 ካሣ ተከፋዮች ክልሉ በመጀመሪያ አጥንቶ ካፀደቀው ብር 7,347,757.30 ውስጥ ብር 4,049,779.00 በመቀነስ ብር 3,279,978.30 ብቻ የከፈለና ለሌሎች በጥናቱ ውስጥ ለሌሉ 6 ተነሺዎች ብር 399,706.32 ካሣ መከፈሉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል።
የካሣ ክፍያ በበጀት ከፀደቀው ሊቀነስ የቻለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዕቅድ ያስቀመጠውን የካሣ ተመን እንዲቀንሱ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት መፈፀሙን፤ ካሣ ተከፍሏቸው ከተነሱ በኋላ እንደገና ተመልሰው የሚሠፍሩ ነዋሪዎችን በተመለከተም ተነሺዎች ካሣው አንሶናል፣ ተተኪ ቦታ አልተሰጠንም የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን በማንሳት ተመልሰው የሚሠፍሩ መሆኑን አቶ ሰለሞን ደስታ አስረድተዋል።
የዩኒቨርስቲዎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ለባለይዞታዎች ካሣ ተከፋዮች የግል አካውንታቸው ማስገባት እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ቢገልፅም መመሪያው ተጥሶ ለ468 ባለይዞታዎች ለራያ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች በጥቅል በደደቢት ብድርና ቁጠባ ሂሣብ ቁጥር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ፤ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች ለፍቼ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት መምሪያ፣ ለቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች ከፋ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ግዥ፣ ክፍያና ንብረት አስተዳደር እና ለእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተነሺዎች በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት አጠቃላይ ብር 79,925,769.02 እንዲገባ መደረጉ እና እስከ ህዳር 29/2009 ዓ.ም ድረስ ገንዘቡ ያልተወራረደ መሆኑ ግኝቱ አመልክቷል።
◌ The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)
ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በሰጡት ምላሽ ካሣ ለባለይዞታዎቹ እንዲከፈል መመሪያ ተዘጋጅቶ በመመሪያው መሠረት ለተነሺዎች ካሣ እንዲከፈል ቢታቀድም ክልሎች በአንድ ጊዜ ገንዘቡ ለተነሺዎች ቢሰጣቸው በዘላቂ አኗኗራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል በሚልና በሌሎች ምክንያቶች በተነሺዎች በአካውንታቸው ገቢ አለመደረጉን ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር አቅዶና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ የመሥራት ውስንነት መኖሩን፤ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አለመደረጉን ገልፀው የግለሰቦች የካሣ ክፍያ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በወጣው መመሪያ መሠረት በየግል አካውንታቸው ገቢ ሊደረግ እና የግንባታ ፕሮጀክቶች ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በተገቢ መጠን ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ11 ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት ሲያስብ በዕቅዱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በተገቢ ሁኔታ ያለየ መሆኑን፤ ከፌዴራልና ከክልል አካላት ጋር ከፍተኛ የቅንጅት ችግር መኖሩን፤ ከግብዓት ጋር በተያያዘ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ግቢ ሜዳ ላይ ሣር እየበቀለባቸው ያሉ ግብዓቶች እስካሁንም በመኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የካሣ ክፍያዎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ሊፈፀም እና ክፍያዎቹ ለባለመብቶቹ መድረሱን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ በኦዲት ግኝቱ የታዩ ችግሮችን በዕቅድ መፍታትና ማረም እንደሚገባ ጠቅሰው ችግሮቹ በሌሎች ተመሳሳይ ግባታዎች እንዳይደገሙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ምንጭ፦ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.