Home › Forums › Semonegna Stories › ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ (ህወሃት እየፈጠረ ያለው ተግዳሮት)
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 18, 2019 at 1:32 pm #12312SemonegnaKeymaster
ከኢህአዴግ ምክር ቤት ኢህአዴግ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ህወሃት እየፈጠረ ያለውን ተግዳሮት በተመለከተ የሰጠው መግለጫ
ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ህብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም. ከተካሄደው 5ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል። በሁሉም የኢህአዴግ መድረኮች በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት እየተያዘበት የሄደ ሲሆን በየጉባዔዎቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ውህደቱን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይልቁንም በቅርብ ጊዜያት በተካሄዱ ጉባዔዎች ይነሳ የነበረው ቁልፍ ችግር በአፈፃፀሙ ላይ የታየው ከፍተኛ መጓተት ነበር። በተለይ ባለፈው ዓመት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የጥናት ሥራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር ውሳኔ ተላልፏል። በሂደቱ የአጋር ድርጅቶችም ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ውህደቱን በተመለከተ አሉታዊ ገፅታ ያላቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለና ያልተቋጨ በመሆኑ በዚህ ወቅት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሚወጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል እምነት ጉዳዩን በዝምታ ለማለፍ የተሞከረ ቢሆንም የተሳሳቱ መረጃዎች ተደጋግመው ሲወጡ ችላ ማለት ደግሞ ሕዝቡ ውስጥ መደናገርን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለሕዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ህወሃት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያው ስህተት ከድርጅት አሠራርና ዲስፒሊን ጋር የተያያዘ ነው። በድርጅቱ አሠራርና ሕገ ደንብ መሠረት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በማንኛውም አጀንዳ ላይ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የመሰላቸውን አቋም መያዝና በአቋማቸውም ላይ ተመሥርተው ክርክራቸውን መቀጠል የተለመደ ነው።
በ2011 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች አጋርና አባል ድርጅቶች ጥናቱ በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ያለልዩነት ወስነዋል። በውሳኔው መሠረት ተጠንቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ ጥናቱ እንዲዳብርም የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶችም ከውሳኔ በፊት ጥናቱን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ሲሆኑ በዚህ ደረጃ በተካሄዱ የአመራር ውይይቶች ህወሃትም ሆነ ሌሎች አባልና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፤ አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል። የተሰጡት አስተያየቶች ጥናቱን ለማዳበር ወይም ያልታዩ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲዳሰሱ ለማድረግ እንጂ የውሳኔ ወይም የአቋም ጉዳይ ሆነው የሚቀርቡ አልነበሩም። በመሆኑም ይህ አጀንዳ ገና በጥናት ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያገኘበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የመጨረሻ የውህደት ውሳኔም አሠራሩን ጠብቆ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ባለበትና የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ባልተገለፀበት ሁኔታ ህወሃት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅት አሠራርና ዲሲፒሊንን የጣሰ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ መታረም ያለበት ነው።
የመግለጫው ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ይዘቱ ነው። ህወሃት በተለያዩ መግለጫዎቹ ደጋግሞ የሚያነሳው ውህደቱ አሃዳዊ መንግስት ለመመሥረት የታቀደ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ፓርቲው ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ በሚቀየርበት ወቅት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንደሚገፈፍና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ፈርሶ አሃዳዊ ሥርዓት እንደሚመሠረት አድርጎ የሚያቀርበው ሃሳብ ለማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር ለመከራከሪያ የሚሆን ተጨባጭ ነገር የለውም። በመሠረቱ የአንድ ሀገር የመንግስት አወቃቀር የሚወሰነው በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ እንጂ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ የኢህአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም።
ኢህአዴግ ወደ ውህደት መጥቶ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ቢሆን ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን እውን በማድረግ እኩልነትና ፍትህ የነገሰባት፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ይታገላል እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችንንና ሕዝቦችን መብት የሚሸራርፍበት ምንም ምክንያት የለውም።
ጥናቱን ያስጠኑት ህወሃትን ጨምሮ ሁሉም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ሲሆኑ የውህደቱ መነሻ ሃሳብም ሆነ የጥናቱ ውጤት ከአሃዳዊ ሥርዓት ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌለው ሁሉም ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ጉዳዩን ሁሉም የግንባሩ አባልና እህት ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁትና ወደፊት ውህደቱ ቢፈፀም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በግልፅ የሚገነዘቡት ሆኖ ሳለ እንዲህ አይነት የተዛባ መረጃ መስጠት መሠረታዊ ስህተት ነው።
ሌላኛው የመግለጫው ችግር የውህደት አጀንዳውን አሁን ያለው የለውጥ አመራር በድንገት ያመጣው በሚያስመስል መልኩ ማቅረቡ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የውህደት አጀንዳው መነሳት የጀመረው ረዘም ካሉ አመታት በፊት እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ደግሞ በድርጅቱ ጉባዔዎች፣ ምክር ቤትና ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባዎች ቃለ ጉባዔዎች ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ እውነታ ነው። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ሰዓት ተጠናቆ ለውይይት የቀረበው ጥናት የተጀመረው አሁን ያለው አመራር ወደ ኃላፊነት ከመምጣቱ በፊት እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነው። አሁን ያለው የለውጥ አመራር የሠራው ነገር ቢኖር ለረጅም ዓመታት በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየውን ጥናት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለውሳኔ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ማድረስ ብቻ ነው። ስለሆነም በድርጅቱ ስም በሚወጡ መግለጫዎችም ሆኑ አንዳንድ አመራሮች በሚሰጧቸው ማብራሪያዎች የውህደቱን ሃሳብ አዲሱ የለውጥ አመራር በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እንዳመጣው አስመስሎ ለሕዝብ ማቅረብ የተሳሳተ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።
በአጠቃላይ ኢሕአዴግን ወደ አንድ ህብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ የመቀየሩ ሃሳብ ዋነኛ ምክንያቶች አሁን ያለው የግንባሩ አደረጃጀት አባል ድርጅቶች የጋራ አሠራርን በሚጥሱ ጊዜ የድርጅቱ የውስጥ ጥንካሬ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑ፣ የግንባሩ የተጠናከረ ሀገራዊ አንድነት በመፍጠር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግቡን በተሟላ ሁኔታ ማሳካት አለመቻሉ፣ አጋር ተብለው የሚጠሩ ድርጅቶችን ከውሳኔ ሰጪነት ያገለለና የሚመሯቸውን ክልሎችና ህዝቦች አቃፊ ባለመሆኑ፣ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በቀጥታ የድርጅቱ አባል ሆኖ መታገል የሚችልበትን ዕድል የሚሰጥ ያለመሆኑን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖር ታሳቢ በማድረግ እንጂ ህወሃት በመግለጫዎቹ ባስቀመጣቸው ምክንያቶች እንዳልሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደሚገነዘቡት እንተማመናለን።
በተጨማሪም ከዚህ አጀንዳ በተያያዘ በቀጣዮቹ ጊዜያት በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ መዋቅሮች (መድረኮች) የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች የድርጅቱ አሠራር በሚፈቅደው ዲሲፒሊን መሠረት ለመላው የድርጅታችን መዋቅርና ለሀገራችን ሕዝቦች መረጃዎችን የምንሰጥና ግልፅ እያደረግን የምንሄድ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
ምንጭ፦ የኢህአዴግ ገጽ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.