Home › Forums › Semonegna Stories › በጣሊያን ባለሀብቶች የተገነባው ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ተመረቀ
Tagged: መቀሌ, መብራህቱ መለሰ, አሸጎዳ, ኢታካ ጨርቃ ጨርቅ, ጣሊያን
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 19, 2018 at 4:41 pm #8156SemonegnaKeymaster
ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ የተለያዩ የሴት አልባሳት በማምረት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት መላክ መጀመሩን የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቴድርኮ ፍራንቦኒ (Federico Fraboni) ተናግረዋል።
መቀሌ (ኢዜአ)–በጣልያኑ ግዙፍ ኩባንያ ካልዜዶንያ ግሩፕ በ15 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገነባው ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ተመረቀ።
በመቀሌ ልዩ ስሙ አሸጎዳ በተባለ አካባቢ የተገነባው ፋብሪካ በወር 22 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አልባሳትን ለዓለም ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳለው በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል።
ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት የንግድና ኢንዱስቱሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለሰ በክልሉ ከተማ ልማት ንግድና ኢንዳስትሪ ቢሮ የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሃፍቶም ፋንታሁነኝ እና በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ተወካይ ሚስተር ፕትሮ ፓናሮላ ናቸው።
የንግድና ኢንዱስቱሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት በጣሊያን ባለሃብቶች ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ አገሪቱን ከማልማት አልፎ የኢትዮጵያዊያንን ትክክለኛ ምስል ለዓለም ያስተዋውቃል፤ ፋብሪካው ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለሀገሪቱ እድገት ትልቅ ድርሻ ያለውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማበረታታት ከሁሉም የመንግስት አካላት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ዶ/ር መብራህቱ ገልጸዋል።
ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ የተለያዩ የሴት አልባሳት በማምረት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት መላክ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቴድርኮ ፍራንቦኒ (Federico Fraboni) ናቸው።
ፋብሪካ በወር 22 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አልባሳት ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ እና ቀደም ሲል ለሙከራ ሲያመርት መቆየቱን ገልጻው የመጀመሪያ ምርቱንም በቅርቡ ለውጭ ገበያ መላኩን ጠቁመዋል።
———————————————-
———————————————-
በክልሉ ከተማ ልማት ንግድና ኢንዳስትሪ ቢሮ የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ዳሬክተር አቶ ሀፍቶም ፋንታሁነኝ በበኩላቸው ፋብሪካው ለአንድ ሺህ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በመቀሌ አካባቢ ኢታካ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካን ጨምሮ ባለቤትነታቸው የውጭ ባለሀብቶች የሆኑ ሦስት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ምርት መሸጋገራቸውንም አቶ ሀፍቶም ተናግረዋል።
ሌሎች አስር የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም በዘርፉ ለመሰመራት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው በተለያዩ የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
በክልሉ የኢንዱስቱሪ ዘርፍ እንቅስቃሴ ከዚህም በላይ እንዲያደግ የመንግስት ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባም አቶ ሀፍቶም ተናግረዋል።
በፋብሪካው ምረቃ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ተወካይ ሚስተር ፕትሮ ፓናሮላ ክልሉ ሰላም የሰፈነበትና ለሥራ የተነሳሳ የሰው ኃይል ያለው መሆኑ በጣሊያን ባለሀብቶች ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
“በኢትዮጵያና በኢጣሊያ የቆየውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊና ልማታዊ ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ለማጠናከር በጋራ እንሠራለን” ብለዋል።
በፋብሪካው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ወጣት ልኡል ኃይሉ አንዱ ነው።
ፋብሪካው በአካባቢው በመከፈቱ እሱን ጨምሮ በርካታ ወጣት ምሩቃንን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግሯል።
“ኢታካ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ወደምርት ሥራ በመግባቱ የሥራ እድል አግኝቺያለሁ” ያለው ደግሞ ወጣት አወጣሀኝ አለነ ነው።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ከጣሊያን አገርና ከኢትዮጵያ የመጡ ባለሀብቶችና ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.