ኢትዮ ቴሌኮም ለአንድ መቶ ሴቶች በፋሽን ዲዛይን የሙያ መስክ ስልጠና እንዲያገኙ ድጋፍ አደረገ

Home Forums Semonegna Stories ኢትዮ ቴሌኮም ለአንድ መቶ ሴቶች በፋሽን ዲዛይን የሙያ መስክ ስልጠና እንዲያገኙ ድጋፍ አደረገ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #12249
    Anonymous
    Inactive

    አዲስ አበባ (ኢትዮ ቴሌኮም) – ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አንድ መቶ ሴቶች በፋሽን ዲዛይን የሙያ መስክ ነፃ የትምህርት ዕድል መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰጠ።

    ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ዘርፍ ከሚያደርጋቸው የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች መካከል ይህ የትምህርት ዕድል የተመቻቸው ሴቶች በትምህርት፣ በሥራ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መስኮች ከወንዶች ያነሰ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን ከግምት በማስገባት ሴቶችን ማስተማር እና በሥራ ማሰማራት ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ብሎም ለሀገር ያለውን ከፍተኛ ሚና በመገንዘብ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም የዚህ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሴቶችን በመመልመል ሂደት ውስጥ በዋነኝነት የኢኮኖሚ አቅምን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን በተለይም ከፍለው መማር የማይችሉ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት አድርጓል።

    ነፃ የትምህርት ዕድል ፕሮጀክቱ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰልጣኝ ተማሪዎች፣ የኢትዮ ቴሌኮም አስተዳደር (management) እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ባደረጉት ንግግር ተቋማት ገቢያቸውን ከማሳደግ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ የሕብረተሰቡን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

    ኢትዮ ቴሌኮም ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ተቋማዊ አሠራር በማጠናከር፣ እቅድ በማውጣት እና አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ አመራሩና ሠራተኛው ጠንካራ፣ አዎንታዊና በተግባር የሚገለጽ አመለካከት በማዳበር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በሌሎች የሕብረተሰብ ችግሮች እና ፍላጎቶች ዙሪያ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል።

    የነፃ ትመህርት ዕድሉን ያገኙ ሴት ሰልጣኞች የፋሽን ዲዛይን ሙያ ፍላጎት ኖሯቸው በአቅም እጥረት ሳይሰለጥኑ ቢቆዩም በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ዕድሉን ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው እንዲሁም ይበልጥ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረጉን ገልጸዋል።

    የዕድሉ ተጠቃሚ ሴቶችም በሚያገኙት የፋሽን ዲዛይን ሙያ ዕውቀት ታግዘው በቀጣይ ለራሳቸው የገቢ ምንጭ የሚፈጥሩ፣ ለቤተሰባቸው አጋዥ፣ ለአካባቢያቸው ምሳሌ እንዲሁም ለሀገራቸው ኩራት እንደሚሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ያምናል። ሀገራችንም በሀገራዊ ምርቶች እና አገልግሎቶች ወደ ፊት ለመራመድ ከፍተኛ ጥረት የምታደርግበት ወቅት በመሆኑ በዚህ የሙያ ዘርፍ መሰልጠን የወደፊት ብሩህ ዘርፍ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ኢትዮ ቴሌኮም ሙሉ እምነት አለው።

    ኢትዮ ቴሌኮም ትምህርት ለሀገር እና ለማኅበረሰብ ግንባታ ያለውን አገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተጠናከረ መልኩ ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ አስታውቋል።

    ምንጭ፦ ኢትዮ ቴሌኮም / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ለሴቶች ነፃ የትምህርት ዕድል (ፎቶ፦ ኢትዮ ቴሌኮም)


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.