ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአምቡላንስ ድጋፍ አበረከተ

Home Forums Semonegna Stories ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአምቡላንስ ድጋፍ አበረከተ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #9657
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– ኢትዮ ቴሌኮም 980 ሺህ ብር የሚያወጣ የአምቡላንስ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አበረከተ። ድርጅቱ ሠራተኞቹን በማስተባበር አሁን ያበረከተውን አምቡላንስ ጨምሮ በተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራት ድጋፍ ለመስጠት ከማኅበሩ ጋር በትብብር እንደሚሠራ አስታውቋል።

    የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በማኅበሩ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተካሄደው ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት አዲሱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሀፊ ዶ/ር መሸሻ ሸዋረጋ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፥ ሌሎች ተቋማትም ይህንን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊ ወገኖች መኖራቸውንና እነዚህን ተደራሽ ለማድረግ ለስድስት ወር ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶ/ር መሸሻ፥ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የማኅበሩ የበላይ ጠባቂና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት አስተባባሪነት የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

    NEWS: Ethio Telecom and Ethiopian Electric Power to cooperate in sharing transmission lines

    የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፣ ሰብዓዊነት ትልቅ ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ የዚህ ዓላማ አጋር በመሆናችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል። የተቋሙ ሠራተኞችም በየወሩ ከደሞዛቸው ከሚያደርጉት የአባልነት መዋጮ ባሻገር በበጎ ፈቃደኝነት በዓመት ሁለቴ የደም ልገሳ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በሀገራችን ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ማቃለል የምንችለው ስንተባበር በመሆኑ ተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ወ/ት ፍሬህይወት ተቋማቸው ከማኅበሩ ጋር ተባብሮ በመሥራት በቀጣይም መሰል ድጋፎችን ማድረግ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

    የማኅበሩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቦርድ አባልና የረጅም ዓመታት የቀይ መስቀል ቤተሰብ የሆኑት አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች በሰብዓዊ ተግባር ላይ በመሰማራት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    ኢትዮ ቴሌኮም ከ20 ዓመት በፊት በ1000 ብር የድርጅት አባልነት መዋጮ ጀምሮ በየዓመቱ በማሳደግ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በዓመት ለማኅበሩ 100 ሺ ብር ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ከ15000 በላይ ሰራተኞቹ ደግሞ የቀይ መስቀል መደበኛ አባል በመሆን በወር ከ30 ሺ ብር በላይ ድጋፍ ያደርጋሉ። በተጨማሪም የተቋሙ ሠራተኞች ማኅበር እንደተቋም አባል በመሆን በየዓመቱ የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ያደርጋል።

    የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሚሰጣቸው ሰብዓዊ አገልግሎቶች መካከል ነፃ የ24 ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎት አንዱ ሲሆን በዓመት በአማካኝ በአንድ አምቡላንስ ለ3600 ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአምቡላንስ ድጋፍ አበረከተ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.