Home › Forums › Semonegna Stories › ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 7 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
June 24, 2019 at 10:28 pm #11197SemonegnaKeymaster
ማለቂያ የሌላቸው ብዙ ብዙ የውሽት ትርክቶች ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ጥቅምም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ፈጽሞ የማይበጅ፣ እንዲያውም በአማራው ክልልም ሆነ በበርካታ አካባቢዎች በጎጥና በአካባቢም ጭምር ወርዶ የእርስ በእርስ ግጭቶች ሊወልድ የሚችል አደጋ ያዘለ ሁኔታ እያደገ መሆኑን የሰሞኑ ክስተት ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከጥፋትና ከእልቂት ለማዳን ቆም ብለን በሰከነ ሁኔታ ማሰብና መራመድ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን።
(ነአምን ዘለቀ)የአማራ መሰረት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ፥
ዛሬ ከፊታችን ያፈጠጠው መሰረታዊ ጥያቄ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እንደግፍ ወይንም አንደግፍ የሚለው አይደለም። የዛሬው ማዕከላዊ ጥያቄ፣ የዛሬው ዋና ጥያቄ ‘ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትቀጥል ወይንስ አትቀጥል’ የሚለው ነው። አብይ መጣ፣ ከበደ፣ ዋቅጅራ፣ ወይንም ግደይ፣ እቺ ታሪካዊት ሀገር፣ እቺ መከረኛ ሀገር፣ እትብታችን የተቀበረባት፣ የምንወዳት፣ ሌት ተቀን የምንጨነቅላት ኢትዮጵያ ሀገራችን፣ በተማሩ ልጆቹ በተደጋጋሚ የተከዳና የተበደለ፣ በድህነትና በችጋር የሚማቅቀው፣ ነገር ግን ጨዋና ኩሩ የሆነው እብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነት እንዴት ይቀጥል ነው ዋናው፣ መሰረታዊው፣ ማዕከላዊው ጥያቄ፣ የዛሬው ጥያቄ፣ የአሁን ሰዓት ዋነኛ ጥያቄ ይሄው ነው።
ሰሞኑን “ኣማራው ተጠቃ፣ ተበደለ፣ ተገፋ” በሚል ሽፋን፣ በአብይ አህመድ “የኦሮሞ/ የኦዴፓን የበላይነት” ለመጫን እየሠራ የሚገኝ የትሮጃን ፈረስ ተደርጎ በሰፊው የሚነዛው ጥላቻ፣ የሚረጨው ሰፊ መርዝና ቅስቀሳ ሰፊው የአማራ ሕዝብን ጥቅም (በአማራው ክልል ብቻ ሳይሆን በኦጋዴን፣ በሀረር፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በኢሉባቡር፣ በወለጋ፣ ወዘተ… በሌሎች አካባቢዎች የሚገኘውን ከ10 ሚሊዮን በላይ አማራኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ) የአማራውን ሕዝብ ደህንነትና ዋስትና ለማረጋገጥ ምን ያህል እንደሚጠቅም፡ ህልውናውንም እንደምን አርጎ ለማረጋገጥ እንደሚያገለግል ቆም ብሎ የታሰበበት አለመሆኑ ግልጽ ነው።
በትናንሽና ፍጹም የማይናበቡ፣ የጋራ ራእይ፣ የጋራ ስልት (strategy) በሌላቸው በየጎጡ የተደራጁና አማራን እንወክላለን በሚሉ እንደ አሸን የፈሉ ቡድኖች የሚደረገው ይሄው በጣም የከረረ ጥላቻ፣ ማለቂያ የሌላቸው ብዙ ብዙ የውሽት ትርክቶች ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ጥቅምም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ፈጽሞ የማይበጅ፣ እንዲያውም በአማራው ክልልም ሆነ በበርካታ አካባቢዎች በጎጥና በአካባቢም ጭምር ወርዶ የእርስ በእርስ ግጭቶች ሊወልድ የሚችል አደጋ ያዘለ ሁኔታ እያደገ መሆኑን የሰሞኑ ክስተት ያመላክታል። ይህ ደግሞ የሶማሊያ፣ የሊቢያ፣ የሶሪያን እልቂትና መበታተን የሚደግም፣ የሚያስከነዳም የምድር ሲኦል እንደሚፈጥር በተረጋጋ አዕምሮ ልብ ያለው ሁሉ ልብ ሊል ይገባል።
ይልቅዬ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የአማራው ዘላቂ ጥቅም የሚጠበቅበት፣ የሁሉም ሕዝቦች አብሮነት የሚረጋገጥበት፣ የኢትዮጵያ እንድነት የምናስቀጥልበት ሁኔታዎችና መንገዶችን፣ ሰከን ብሎ ማሰብ፣ በስሜት ሳይሆን በስትሪቴጂያዊ አስተሳሰብ፣ በጥበብና በስልት፣ በጋራ፣ ሰጥቶ በመቀበል እንጂ፣ ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ እንደሚራገበው አማራውን እንወክላለን የሚሉ በልዩ ልዩ ቡድኖች የተደራጁም ያልተደራጁም አክራሪ ብሄርተኞች እጅግ በሚያጦዙት መንገድ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል የሮኬት ሳይንስ አውቀት የማያስፈልገው ሃቅ ይመስለኛል።
ሰደድ እሳቱ ሲጀመር እያንዳንዱ ቤት አንደሚያንኳኳ ቆም ብሎ ማሰብ፣ ከሌሎች ሀገሮች ውድመት፣ ውድቀትና፣ ምስቅልቅል መማር ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት ቆም በሎ ማሰብ ብልህነት፣ አስተውሎትም ነው። ስለዚህ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ማዕከላዊ መንግስት የተከፈተውን ምህዳር ተጠቅሞ በሰላማዊ፣ ሕጋዊ፣ ስልታዊና ስትራቴጅካዊ አካሄድ በሰላማዊና በተደራጀ መልክ የአማራውን ሕዝብ ጥቅም፣ ደኅንነት ለማሰጠበቅ መንቀሳቀስ እንጂ፥ የሰፈር የጦር አበጋዞች (በሶማሊያና በሊቢያ እንዳየነው “warlords”)፣ ከሕግና ከስርዓት ውጭ የራሳቸውን ፍላጎት በጉልበት ለመጫን የሚፈልጉ አፈንጋጮችን (በሶሪያ እንደተከሰተው “rogue military commanders”) በማጀገን የአማራውን ሕዝብ ተገፍቻለሁ፣ ተጠቅቻለሁ ብሎ እንዲነሳሳ ሰፊ ቅስቀሳ ማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው፣ የአማራውን ሕዝብንም ሆነ፣ የአማራው ማኅበረሰብ በደም፣ በሕይወቱ፣ በላቡ ገብሮ፣ ለግንባታዋ ብዙ የተዋደቀላት ትላቋና ታሪካዊቷ ኢትዮጵያን የማይበጅ፣ ወደ ጥፋት፣ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት፣ አልፎም ወደ ውድመትና ወደ መበታተን ሊያደርሰን የሚችል ሂደት እየተመለከትን ነው።
በዚህ ሁሉ ትርምስ ደግሞ ዛሬ የሚፈነጥዘው፣ ይህን ሰፊ ትርምስ (turmoil) ለራሱ በሚገባ እየተጠቀመ የሚገኘው፥ እንደ አንድ ሰው የቆመው፣ እስከ አፍንጫው የታጠቀውም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ብቻ ነው። ሌላው ተከፋፍሏል፣ በአብይ አህመድ ላይ በሚወርደው የጥላቻ ውርጅብኝም ሀገሪቷን እንደ ሙጫ አጣብቆ ደካማ ቢሆንም የያዘውን ስርዓተ መንግስት (state)፣ ማዕከላዊ መንግስቱንም ለማዳከም ብዙ የድንጋይ ናዳ አየወረደ ነው። በየዕለቱ በተደራጀም በአልተደራጀም መልኩ እየተደረገ የሚገኘው ይሄው ነው።
ሕዝብን እርስ በእርስ ሊያባላ፣ ሊያጫርስ የሚችል፣ ምንም አማራጭ ሃሳብ፣ ራእይና፣ ድርጅትም ሆነ ስትራቴጂ ለማቅረብ የማይችሉ፣ ነገር ግን አማራውን እንወክላለን የሚሉ፣ እንዲሁም በአብይ አህመድ ላይ የግል ጥላቻና ጥርጣሬ ያላቸው በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ጭምር ተሳታፊ የሆኑበት ይሄው በከፍተኛ ስሜት በማጦዝ፣ የተገፊነትን ስሜት በመቀስቀስ ላይ የተመሰረተ ሰፊ ዘመቻ ያነጣጠረውና እየሄደ ያለው በዚሁ ግብ ላይ ነው። የእነዚህ ቡድኖች ምንም መናበብም ሆነ፣ የጋራ አማራጭ፣ እንዲሁም ለሀገራችንና ለሕዝባችን አሻግሮ የሚያይ ራእይ ማቅረብ ያማይችሉ፣ እርስ በእርሳቸው እንኳን ተቀምጠው በአግባቡ በምክኒያታዊነት መነጋገርና መደማመጥ የማይችሉ፣ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ኃይሎች የሚገፋውና የሚረጨው መርዝ ሁሉንም (እነሱንም ጨምሮ) ወደ ፍጹማዊ ኪሳራ፣ የዜሮ ድምር ፓለቲካ (zero-sum game) የሚወስድ፣ ማንም ምንም ወደማያተርፍበት የሲኦል መንገድ አገራችንንና ሕዝባችንን እየገፋ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዛሬ ላይ በሚገባ መገንዘብ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ የደረሰን ይመስለኛል። ነገ በጣም ይዘገያል የዘገየ (too little too late) ይሆናል።
ከዚህ አሳፋሪና ለሀገራችን ህልውና ብሎም ለኢትዮጵያ 105 ሚሊዮን ሕዝብ አብሮነት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ቀጣይነት እጅግ አስጊ ሁኔታ በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅት አሸናፊ የሚሆነው ማነው? ሁሉንስ ድልና ወርቅ አፋሽ የሚሆነው ማነው? ብቸኛ ተጠቃሚስ ይኖራል ወይ? በሰላም ደሴት በደስታና በፍሰሃ ሊኖር የሚችለውስ ማነው? ስለእውነት፡ ስለሀቅ ለመናገር ማንም እንደማይሆን፣ ማንም እንደማይተርፍ በእርግጠኝነት መተንበይ ይቻላል። ሁላችንም ተያይዘን ወደ እልቂት፣ ወደ ሁለንተናዊ ውድቀት፣ ወደ ሲኦል እያዘገምን ይመስለኛል።
ስለዚህ ወግኖቼ፥ ቆም ብለን ማሰብ ብልህነት ነው። ነገን ማሰብ፣ በተረጋጋና በምክንያታዊነት ዛሬን በትዕግስትና በስልት መራመድ አሰፈላጊና ወሳኝም ናቸው። የአማራውንም ጥቅምና ደኅንነት፣ የሌላውን ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰቦች/ብሄሮች፣ አብሮነት፣ የአማራውንም ሆነ የሌላውን እኩልነት፣ መብት፣ ደህንነት፣ ለማምጣት በጥንቃቄ፣ በሕግ አግባብ፣ በሰላማዊ መንገድ፣ አስቦ፣ በአስተውሎ መራመድ የነገን ውድመት፣ የሀገር መበታተን፣ የሕዝብንም እልቂት የሚከላከል ሁሉም ሕዝቦች በጋራ በሰላም፡ በዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነት፡ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን የሚያረጋግጥልን ብቸኛ መንገድ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ሁሉም የአማራ መሰረት ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በውጭም በሀገር ውስጥም ሊያጤነው የሚገባ ይመስለኛል። የመጨረሻው ደወል እያቃጨለ መሆኑ እየተሰማኝ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ሁሉም ሕዝቦች፣ ማኅበረስቦች፣ በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በሕግ የበላይነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ የአማራ መሰረት ያለው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጥሞና አስበን፣ አስተውለን፣ አቅደን መንቀሳቀስና ሀገራችንን ከጥፋት የማዳኛው ወቅት አሁን ነው፣ ዛሬ ነው።
እግዚአብሔር ሀገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን፤ ስላሙን ያውርድልን።
ነአምን ዘለቀ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.