Home › Forums › Semonegna Stories › ኤርሚያስን የትኛው “ወንጀል” ሊያሳስረው ይችላል?
Tagged: መለስ ዜናዊ, ሜቴክ, ኤርሚያስ አመልጋ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
June 18, 2019 at 2:35 am #11123AnonymousInactive
ኤርሚያስ ሊታሰር የሚችለው ከፈጠራና ሙግቱ በተያያዘ እንደሆነ ትልቁን ግምት መውሰድ ይቻላል። የኤርሚያስ ትልቁ “ወንጀል” ገዥዎቹና ገዥዎችን ተጠልለው የከበሩትን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ስለሚሞግትና ስለሚወዳደራቸው፣ ስጋት ስለሆነባቸው ይመስለኛል።
ኤርሚያስን የትኛው “ወንጀል” ሊያሳስረው ይችላል?
(ጌታቸው ሽፈራው)ኤርሚያስ አመልጋን የማውቀው ሚዲያ ላይ ነበር። 2008 ዓ.ም. ክረምት ላይ ያልጠበኩት ቦታ አገኘሁት። ማዕከላዊ ጠባብ ክፍል ውስጥ። ትኋን ከጣራው የሚዘንብበት “ሸራተን” የሚባል አስቀያሚ እስር ቤት ውስጥ ነው የሆነች ጥግ ይዞ ያገኘሁት። ሀብታሞች እስር ቤት ሲገቡ ትሁት ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። የኤርሚያስ ግን ሳይለይ አይቀርም። የምሩን ይመስለኛል። ብዙ ሰው ጓደኛው ነው። ወጣቶች ጓደኞቹ ናቸው። ሀብታሞቹ ፈልገውት ይመጣሉ። እሱ ግን በአብዛኛው ውሎው ከሌሎቹ ጋር ነው።
ከምንም በላይ የገረመኝ በዛን ወቅት የነበረው የፖለቲካ ዝንባሌው ነው። ወቅቱ 2008 ዓ.ም. ነው። በዚህ ወቅት ብዙ ጉዳይ ይበላሽብኛል የሚል ሀብታም የማይነካውን አጀንዳ ኤርሚያስ አይፈራውም። ውሎው በሽብር ከተከሰሱት ጋር መሆኑ አይደለም። ሰላይ በሞላበት እስር ቤት በወቅቱ በሽብር የተፈረጁት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መካከል “ማን ሊጠቅመን ይችላል? እንዴትስ ከግብ ይደርሳሉ? ምን ይደረግ?” የሚል ውይይት ላይ በቀጥታ ይሳተፍ ነበር። በፖለቲካ አመለካከታቸው የተለያየ ጠርዝ ላይ የተቀመጡ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችንና አባላትን፣ ግለሰቦችን ሰብስቦ ያወያይ ነበር። የውይይት መሪው ራሱ ነበር። ያከራክር ነበር። በዛ ጠባብና ማንም ውይይቱን በሚሰማበት ቤት መድረክ መሪው ኤርሚያስ ነው።
በአንድ ክፍል ውስጥ በነበረችን ጥቂት ቆይታ እንዳጫወተኝ አቶ ኤርሚያስ መለስ ዜናዊንም በኢኮኖሚ ፖሊሲው በደንብ ሞግቶታል። መለስ የኤርሚያስን ፈጠራ ችሎታ ባይክድም ሙግቱን አልወደደለትም። እየቆዩ ግን ገዥዎቹ ፈጠራውንም አልወደዱለትም። አብዛኛው አሠራራቸው ጋር ይጋጫል። ለአብነት ያህል ዘመን ባንክን የመሰረተው ብዙ የግንባታ ወጭ ሳያወጣ በቴክኖሎጅው የትም እንዲያገለግል ነው። ኢህአዴግ ግን የትኛውም ባንክ በዓመት 5 በመቶ የሚሆን የቅርንጫፍ ማስፋፊያ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ፖሊሲ አውጥቷል። ከዛም ሲያልፍ ብዙ ሴራዎች እንዳሉ ኤርሚያስ በግልፅ ይናገራል።
ኤርሚያስ በእስሩ ወቅት ችግር ቢገጥመውም በቀላሉ ሲያልፋቸው አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ዐቃቤ ሕግ ሚሊዮን ብሮችን የሚያስይዘበትን የዋስትና መብቱን (መጨረሻ ላይ በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን መሰለኝ የተለቀቀው) ሲነፍገው እስረኞች እንደሚሰማቸው ብስጭትና ንዴት አይታይበትም። እስረኞች በግፍ ፍትሕ ለተከለከለ እንደሚቆጩት ለእሱም ሲቆጩና ሲናደዱ “ምን አናደዳችሁ?” እያለ የሚቀልድ ሰው ነው። ብርታቱ በፖለቲካ ጉዳይ የሚታሰሩ የተወሰኑ ብርቱዎች የያዙትን እንጅ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ተከሰው እስረኛውን እንቅልፍ ከሚከለከሉት ብዙሃን ነጋዴዎች ጋር የሚመሳሰል አልነበረም።
◌ ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
ኤርሚያስ ለብዙ ነገሮች ተስፋ ቆርጦ “ሽብርክ” አለማለቱ በገዥዎች የተወደደለት አይመስለኝም። ፈጠራው የተወደደለት አይመስለኝም። በእርግጥ ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ ጎበዝ ነጋዴዎች ይኖራሉ። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ የራሳቸውን ፈጠራ፣ ብቃትና ሀብት በሌላ ይሁንታ ጭምር እንዲተዳደር የሚፈልጉ ናቸው። ኤርሚያስ ይህ የሚፈቅድ ሰው አይመስልም። በትንሽ ትዝብቴ ፈጠራውን በገዥዎች ይሁንታ የሚያስተዳድር እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ።
ከራሱ ፈጠራ ባለፈ ቤተ መንግስት ገብቶ እነ መለስን ፖሊሲያዎቸው ኢኮኖሚውን የማያራምድ፣ ለሀገር ኪሳራ መሆኑን ሞግቷል። በዚያ ጨለማ ወቅት፣ በዚያ ብዙ ባለሀብት ባሽቃበጠበት ወቅት እነ መለስን የሞገተ ሰው የዛሬዎቹን ከመሞገት ወደኋላ እንደማይል ግልፅ ነው። በፖሊሱ ጉዳይ ከመተቸት ባለፈ የወቅቱ ገዥዎችም እንደ ድሮዎቹ ባለሀብቱ ወደራሳቸው ቀየ እንዲጎርፉ ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ኤርሚያስ ፍላጎት የነበረው አይመስልም። ኤርሚያስ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ የመረጣቸው ቦታዎች እንደነበሩ ሲነገር ቆይቷል። ኤርሚያስ በዚህ የእፎይታ ይመስል የነበረ “የለውጥ” ወቅት በአዲስ ፈጠራ ለመምጣት ጥረት እያደረገ እንደነበር ተገልጿል። ብዙ ዕቅዶች እንዳሉት ያወራ ነበር። ለብዙዎቹ ሀብቶች ፈተና ነው። ገዥዎችንም ይሞግታል። እነሱ ወደፈለጉት ቦታ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስም ፈቃደኛ አይመስልም። የኤርሚያስን እስር ሳስታውስ የሚመጡልኝ እነዚህ የገዥዎቹ ወጥመዶች ናቸው። እንጂማ ኤርሚያስ ከአረብ ባለሀብት የተሻለ ሀገሩን መጥቀም የሚያስችል እውቀት አለው። ገንዘቡን ባያፈስ እንኳ ከእነ ፍራንሲስ ፉኩያማ የተሻለ የሀገሩን ባህልና ጥቃቅን ክፍተቶች የሚረዳ ጥሩ አማካሪ መሆን ይችል የነበር ሰው ነው። በኤርሚያስ ላይ እንደ ችግር የተወሰደበት በውጥንቅጥና በኪሳራ ወቅትም እሠራለሁ የሚልበት ሥነ-ልቦናው ይሆናል።
በአንድ ወቅት ስንከራከር ሊያሳምነኝ ያልቻለ ሙግት ነበረው። የገዥዎቹን ድርጅቶች አቅልሎ ነው የሚያያቸው። ሜዳው ከአፈና እና ወከባ ከተላቀቀ በቀላሉ ከስረው የሚወጡ እንደሆኑ ነው የሚናገረው። በመንግስት ድጎማ፣ ሙስና፣ ሌሎቹን በማፈን እና በገዥዎች ትብብር ትርፍ የሚያግበሰብሱት ተቋማት እውነተኛው ስርዓት ሲመጣ አፍታ ሳይቆዩ ከሜዳው እንደሚወጡ ነው የሚናገረው። የሰው ኃይልን በገፍ አስገብተው ጉልበት እየበዘበዙ የሚያጋብሱት ድርጅቶች የሰለጠነና በእውቀት የሚመራ ጋር ተወዳድረው እንደማይዋጣላቸው ነበር የሚናገረው። በወቅቱ የኢፈርትን ጡንቻ እያሰብኩ ኤርሚያስ የዋህ የሆነ ይመስለኝ ነበር። ከእነዚህ ግዙፎች ጋር ተወዳደሮ ማሸነፍ እንደሚችል በድፍረት ሲናገር ወኔውን አድንቄያለሁ። ይህ ወኔ ግን አግበስብሰው ለሚያተርፉትና አትራፊዎቹን ለያዙት ፈተና ይሆናል። ሳስበው ኤርሚያስ ትክክል ነበር። እነ ሜቴክን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ዛሬም ሌሎች ባለሜቴኮች አሉ። ኤርሚያስ ለእነዚህ ገንዘብ ከየትም አምጥተው በገዥዎች እገዛ ለሚያተርፉት ሰዎች ስጋት ነው። ኤርሚያስ ከእስር እንደተፈታ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ጉዳዮች ያወራ ነበር። አንደኛው የኢኮኖሚ ተንታኝ ቡድን ማዋቀር ነው። መሰል ቡድን አዋቅሮ በተሻለ ሜዳ ልወዳደር ቢል በገዥዎቹ እገዛ ሚያተርፈው ስጋት ሊሆን ይችላል። ኤርሚያስን ሊያሳስረው ከሚችሉት ነገሮች መካከል ሳብሰለስል የሚመጡልኝ መሰል ጉዳዮች ናቸው።
ሁሉም እስረኛ ነፃ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ሆኖም በዚህ ዘራፊ የገዥዎቹ ቀኝ እጅ ሆኖ በሚኖርበት ሀገር ኤርሚያስ መታሰር አይገባውም ለማለት ሞራል አናጣም። ዘራፊዎች የገዥዎች መመኪያ ሆነው በሚኖሩበት፣ ዘራፊዎች የገዥዎች ከለላ በሚደረግላቸው ሀገር ኤርሚያስ በወንጀል ታሰረ ለማለት ክፉ ሕሊና ይጠይቃል። ቢያንስ ገዥዎችንና ገዥዎችን ታክከው ያገኙትን ገንዘብ እንጅ እውቀታቸውን ተማምነው፣ በእውቀት ተመርተው መነገድ ከማይችሉት አጎብዳጆች የተሻለ መሆኑን መካድ አይቻልም። ቢያንስ ቢያንስ የውጭ ባለሙያዎችን ያህል “አማክረን” ተብሎ ብዙ ሳይለመን ምክር የሚለግስ፣ ለሀገር የሚጠቅም መሆኑን መካድ አይቻልም። ከውጭ እንደሚመጡት አማካሪዎች ብዙ ገንዘብ ሳይጠይቅ የወልስትሬት (Wall Street) ልምዱን በቀናነት ለሀገሩ ሊያካፍል እንደሚችል መካድ አይቻልም። ኤርሚያስ ሊታሰር የሚችለው ከፈጠራና ሙግቱ በተያያዘ እንደሆነ ትልቁን ግምት መውሰድ ይቻላል። የኤርሚያስ ትልቁ “ወንጀል” ገዥዎቹና ገዥዎችን ተጠልለው የከበሩትን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ስለሚሞግትና ስለሚወዳደራቸው፣ ስጋት ስለሆነባቸው ይመስለኛል። ኤርሚያስን የፈለገ ወንጀል ሠራ ቢሉን ወንጀለኞች በሚሸለሙበት ሀገር፣ ዘራፊዎች ለገዥዎች በማጎብደዳቸው “ነፃ ሆነው” በሚኖሩበት ሀገር የሚያሳስረው ወንጀልን ለመገመት የሚከብድ ነው።
ኤርሚያስ ነፃ ይመስለኛል። ነፃ እንኳን ባይሆን ከአጎብዳጆቹ አንፃር ሊሸለም የሚገባው ሰው እንደሆነ አምናለሁ። ኤርሚያስ ባይታሰር ለገዥዎቹ ባይጠቅም፣ ለሀገሩ ብዙ ብዙ ይጠቅማል።
ኤርሚያስን ፍቱት!
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.