እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ ― ታማኝ በየነ

Home Forums Semonegna Stories እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ ― ታማኝ በየነ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10525
    Semonegna
    Keymaster

    እንደ አንድ ዜጋ እጠይቃለሁ ― ታማኝ በየነ

    ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስት፤

    እኔ በደረሰኝ መረጃ ከትናንት ጀምሮ በወሎ ከሚሴና በሽዋ አጣዬ በደረሰ ግጭት ንጹሃን ዜጎች እየሞቱ ነው፡፡

    ለመሆኑ ሰላም የነበር አካባቢ በአንዴ ወደ ጦርነት ቀጠና እንዴት ሊለወጥ ቻለ?

    የአማራ ክልል መንግስት በእካባቢው የታጠቁ ሃይሎች ሲገቡና ሲወጡ አላየም ነበር?

    የኦሮሚያ ክልል መንግስትስ ከራሱ ኃይል ውጭ የታጠቀ ኃይል ሲያይ ‘ማን ነህ?’ ብሎ አይጠይቅም ወይ?

    ኦዴፓ (የኦሮሞ ዲሚክራሲያዊ ፓርቲ) እና አዴፓ (የአማራ ዲሚክራሲያዊ ፓርቲ) በእርግጥ እየተነጋገራችሁ ነው የምትሠሩት? ከሆነስ የአንድ ንጹህ ዜጋ ህይወት ከማለፉ በፊት ለምን ግጭቱን ተነጋግራችሁ አትፈቱትም ነበር?

    የፌደራል መንግስት እንደ እኛ ውጭ እንዳለነው እኩል ነው ግጭቱን የሰማው?

    በአጠቃላይ ለተፈጠረው ቀውስ ከፌደራል መንግስቱና ከሁለቱ የክልል መንግስታት ውጭ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ የለም።

    በአጠቃላይ በየቦታው የሚታዩት ግጭቶች ነገን አስፈሪ እያደረጉት ነው፡፡ መንግስት ሁሉንም በእኩል ዓይን አይቶ በጥፋተኛው ላይ የማያዳግም እርምጃ ካልወሰደ ወደ ፈራነው እልቂት እንደምንገባ ለመናገር ትንቢት ተናጋሪ መሆን አያስፈልግም፡፡

    ገና በጠዋት ‘የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዘር ፖለቲካ መሠረት ሲጣል አይበጀንም!’ ብዬ አደባባይ የወጣሁት የዘረ ፖለቲካ መጨረሻው ዛሬ የምናየው በእጅጉ በከፋ ሁኔታ ነገ የምንጋፈጠው መሆኑን በመረዳት ነበር።

    ዛሬ የዘር ፖለቲካ በድርስ ዘዋሪ አፍላ ጎረምሳዎችም፣ እድሜ በተጫናቸው በችግሩ አምጪ አዛውንቶችም በአስፈሪ ሁኔታ እየተራገበ እሳቱ ደግሞ በየቀኑ አገር የቆመችበትን ምሶሶ እየለበለበ የዜጎችን ነፍስ እየቀጠፈ ነው።

    አስገራሚው ነገር በተመሳሳይ ወቅት ያልተማርንበት የሩዋንዳ የዘር ፍጅት መታሰቢያ ለ25ኛ ጊዜ በዓለም መድረክ እየታወሰ ነው። እኛ እንደሌሎቹ ካለፈው መማሩ ቢሳነን ዛሬ እየሆነ ባለው በራሳችን ውድቀት ለመማር እንኳን ዝግጁ የሆንን አንመስልም።

    እርግጥ ነው መንግስት በቅርቡ የአገራችን መሠረታዊ ችግር የምንከተለው የብሔር ፖለቲካ ነው ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ በግልፅ ማሳወቁ የተስፋ ምልክት ሆኖ ሊታይ ይችላል።

    ይህ በራሱ ግን ከዛሬው እልቂት የሚታደገን አይደለምና የፌደራል መንግስቱም ሆነ የሁለቱ ክልል መንግስታት በአፋጣኝ ይህን ሁኔታ ቀልብሰው ከዚህ በላይ ሌላ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲከላከሉ ይህንን ሰይጣናዊ ተግባር የሚፈፅሙ አካላትንም በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ እንደ አንድ ዜጋ ለመጠየቅ እወዳለሁ።

    ኢትዮጵያዊው ታማኝ በየነ (አሜሪካ)

    ምንጭ፦ ECADF Ethiopian News / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተያያዥ ዜና፦ አጣየ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ እና አካባው በሚኖሩ ዜጎች ላይ የታጠቁ ኃይሎች እያደረሱት ያለው ኢ-ሰብአዊ በደል

    ታማኝ በየነ


     

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.