Home › Forums › Semonegna Stories › በኦሮሚያ ክልል በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!
- This topic has 1 reply, 1 voice, and was last updated 4 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
July 6, 2020 at 10:42 pm #15031AnonymousInactive
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአፋጣኝ ይቁም!!
(ያሬድ ኃይለማርያም*)
በ1994 እ.ኤ.አ. ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዋናነት የመሩት ሁለት ሬድዮ ጣቢያዎች ነበሩ። አንዱ በመንግሥት ስር የነበረው ሬድዮ ሩዋንዳ (Radio Rwanda) የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው የእልቂቱ አነሳሽና ቀስቃሽ የነበረው Radio Télévision des Milles Collines (RTLM) ተብሎ የሚጠራው ጣቢያ ነበር። ይህ ጣቢያ በወቅቱ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ስለነበር በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን እና የቀኝ አክራርሪ የሆኑትን የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻዎችን (Interahamwe militia) በቀላሉ ወደ ጥላቻ በመንዳት በመምራት እና እልቂት እንዲፈጽሙም በማነሳሳት ትልቅ ሥራ ሠርቷል። ይህ ጣቢያ ከእልቂቱም በፊት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል ጥላቻን ሲሰብክ ቆይቷል።
ዛሬ ደግሞ ተራው የእኛ በሚመስል ሁኔታ እጅግ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ለዓመታት ጥላቻን ለኦሮሞ ወጣቶች እና ለኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ሲሰብክ የነበረው OMN የተባለው ሚዲያ የወንድማችንን ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ተከታታይ የአመጽ እና የእልቂት ጥሪዎች እና ቅስቀሳዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ልክ የሩዋንዳው RTLM እንዳደረገው ሁሉ ጥሪው ክልሉ ውስጥ ላሉ ሥራ-አጥ ወጣቶች እና በሽኔ ስም ለሚጠሩት ሚሊሺያዎች ነበር። በዚህም እጅግ ለመስማትና ለማየት የሚሰቀጥጡ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲፈጸሙ ተደርጓል። ሰዎች እቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከነቤተሰቦቻቸው በእሳት ጋይተዋል፤ ህጻናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በስለት እና በቆንጨራ ተቆራርጠው ተገድለዋል፤ እናት ከህጻን ልጇ ጋር በአንድ ገመድ ታንቃ ተገድላለች፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ወድሟል፤ ብዙዎች ከቤታቸው ሸሽተው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ተደብቀዋል።
አንዳንድ እማኞች በመገናኛ ብዙኃን ምስክርነታቸውን እንደሰጡት እና እኛም ማረጋገጥ እንደቻልነው ለጥቃት የተሰማሩት ኃይሎች በቂ ዝግጅት ያደረጉ፣ የተለያዩ የጥቃት መሣሪያዎችን የያዙ እና የጥቃት ዒላማ የሆኑ ሰዎችን ስም እና አድራሻም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል። ነገሩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በክልሉ ውስጥ ያሉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ይህ ሁሉ እልቂት ሲፈጸም ድርጊቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። በአሜሪካ ድምጽ (ቬኦኤ) እና አንዳንድ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም በተወሰኑ ቦታዎች የመንግሥቱ ታጣቂዎች ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ጥቃት ሲፈጸም እያዩ ዝምታን መርጠው መቆየታቸው ነው። በሩዋንዳም የዘር ማጥፋት ጥቃት ሲፈጸም የሆነው ይሄው ነበር። እነዚህ ኃይሎች በምንም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም። በኦሮሞ ሕዝብ መሃል የበቀሉ እንክርዳዶች ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ቡድኖችን እና ነገሩን በቸልታ ሲያዩ በነበሩ የክልሉ ኃላፊዎች ላይ በቂ ምርመራ ሊካሔድ እና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
OMN አዲስ አበባ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ቢዘጋም ተመሳሳይ የእልቂት ጥሪዎችን ከሀገር ውጭ ባሉ ባልደረቦቹ በኩል ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ ይህ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ አየር ላይ ያዋላቸውን እና በዩቲዩብ (YouTube) የተላለፉ ዝግጅቶቹን ከአየር ላይ እያወረደ እና መረጃዎችን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፦
(፩ኛ) የእነዚህ የእልቂት ጥሪዎች ቅጂዎቻቸው ጣቢያው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት እጅ ስለሚገኙ እና የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲውም የእነዚህ ቅስቀሳዎች ቅጂ እንዳለው ባለሥልጣኑ ስለተናገሩ ጣቢያው መረጃ ለማጥፋት እያደረገ ያለው ጥረት ይሳካል ብዬ አላምንም። ነገር ግን እነዚህ መረጃዎች በመንግሥት በኩል በቂ ጥበቃ ተደርጎላቸው በክልሉ ውስጥ ለተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ያላቸው አስተዋጽኦ በአግባቡ ሊመረመር ይገባል፤
(፪ኛ) በOMN የተላለፉ የዘር ተኮር ቅስቀሳ ቪዲዮዎች እና ዘገባዎች በእጃችው ላይ የሚገኝ እና ጉዳዩ የሚያሳስባችው ግለሰቦች፤ እንዲሁም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና አንዳን አካባቢዎች የተፈጸሙ ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ያላችሁ ሰዎች በዚህ የኢሜል አድራሻ end.empunity.eth@gmail.com እንድታቀብሉን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ዘር ተኮር ጥቃት ይቁም!
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
July 6, 2020 at 11:26 pm #15035AnonymousInactiveበኦሮሚያ ክልል “ከአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው” በተባሉ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ― የአሜሪካ ድምፅ
በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ተወላጅ ናቸው በተባሉ ዜጎች ላይ በተነጣጠረ ጥቃት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈፀመው “ከአንድ ብሔር የመጡ ናቸው” የሚሉ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ቢሆንም፥ ሕብረተሰቡ የተጋባና የተዋለደ በመሆኑ ተጎጂ ከሆኑት ውስጥ ከተለያየ ብሔር የተወጣጡ ሰዎች መሆናቸውን ነዋሪዎችም፣ የዞኑ አስተዳዳሪም ተናግረዋል።
ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ ገላን ኮንደሚኒየም አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለውን ዝነኛውን የኦሮሚኛ ቋንቋ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እጅግ አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ማጉደል፣ ዘረፋና በከፍተኛ ሁኔታ ንብረት ማቃጠል መከሰቱንም ተጎጂዎችና የዓይን እማኝ መሆናቸውን የተናገሩ ለአሜሪካ ድምፅ (ቪኦኤ) ገልፀዋል።
አንዳንዶቹ ግድያዎች በደቦ የተፈፀሙ ሲሆኑ፥ አንዳንዶቹ ግን በሰለጠኑ እና ተኩሰው በማይስቱ ታጣቂዎች የተፈፀሙ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአሜሪካ ድምፅ ቤተሰቦቻቸው ፊት ለፊታቸው እደተገደሉባቸው የሚናገሩ፣ ንብረታቸው እንደተቃጠለባቸውና ያለ መጠለያ መቅረታቸውን የሚገልፁ በተለያዩ ከተማ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎችን ያነጋገረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት (ሰኔ 29 ቀን) በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ከጥቃት ከተረፉት መካከል የተወሰኑትን አስደምጧል።
በሌላ በኩል የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጀማል አልዩ በአርሲ ዞን ውስጥ እርሳቸው ከሚያስተዳድሯቸው 25 ወረዳዎችና ሦስት ከተሞች መካከል በስድስቱ ውስጥ በተፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገፀዋል። ድርጊቱ በአካባቢው ከነበረው ፖሊስ አቅም በላይ እንደነበርና የፀጥታ አባል ጭምር መገደሉን አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተለያዩ ከተሞች ጥቃቶቹ መፈፀማቸውን አምነዋል።
ድርጊቱ የተፈፀመው በሁለት ብሔሮች መካከል የተካረረ ፀብና ግጭት በመቀስቀስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማቸው ባደረጉ አካላት ነው ሲሉም ከግጭቱ ጀርባ ሌሎች ቡድኖች እንዳሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። መንግሥት ይህንን በአስቸኳይ በመረዳት የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱን ከክልል የፀጥታ ጥበቃ አባላት ጋር በማዋቀር የመከላከል ሥራ በመሥራቱ እንጂ ከዚህም የባሰ ጥቃት ይደርስ ነበር ሲል መንግሥት መግለጫ ሰጥቷል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን እስካሁን የ145 ሰላማዊ ዜጎች እና የ11 የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት በድምሩ የ156 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ደግሞ በአዲስ አበባ የሁለት የፀጥታ ኃይሎችና የስምንት ሲቪሎች በድምሩ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አረግጋጠዋል። በአጠቃላይ ከመንግሥት የተገኘው መረጃ 166 ሰዎች በቦምብ፣ በጥይት፣ በድንጋይና በመሳሰሉት ሕይወታቸው ማለፉ ይጠቁማል።
ምንጭ፦ የአሜሪካ ድምፅ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.