Home › Forums › Semonegna Stories › ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 10 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
March 21, 2019 at 4:26 pm #10339SemonegnaKeymaster
ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች !!
አገራችን ኢትዮጵያ 76 ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት ታላቅ አገር ነች። የሕዝባችን አብሮ የመኖር እሴት የሰው ልጆች መደበኛ ማኅበራዊ ግንኙነት ተሻግሮ በደም ዝምድና ተጋምዶ በባህል ተሳስሮ ላይለያይ ተቆራኝቷል። ይህ ህብረት የብሄር ማንነት እና የእምነት ልዩነት ሳይለያየው ለሺህ ዓመታት፣ ሺህ ችግሮችን ተጋፍጦ ይሄው ዛሬም ድረስ በጋራ ዘልቋል።
የዚህ አኩሪ ታሪክ ጉዞ አልጋ ባልጋ ያልነበረ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሕዝባችን የሚያነሳቸው የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን መንግሥታት በመታገል ለመብቱ የተከራከረበት ወቅትም በርካታ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብትና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎች ምክንያት በአገሪቱ ለውጥ አንዲመጣ አድርጓል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያዊንን እና ሌላውን ዓለም ያስደመሙ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከተማችንም ዘመን ተሻጋሪና ተጨባጭ ውጤቶች እየተከናወኑና ቀደም ሲል ሕዝባችን ያነሳቸው የነበሩ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የልማትና መሰል አጀንዳዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል።
በመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ የሚመራው የከተማችን አስተዳደር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መርሆዎችን ተከትሎ የአዲስ አበባ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማካሄድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸው የከተማው ነዋሪ የሚመሰክረው ሃቅ ነው።
በሌላ በኩል የከተማችን ነዋሪዎች ሕገ-መንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በከተማው ሕዝብ ተሳትፎ ወኪሎችን በመምረጥ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ። ይህ ሲባል ሕዝቡ ከአስፈፃሚው አካል ጐን ሆኖ ባያግዝና ባይሳተፍ ኖሮ አሁን የተገኘውን ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ነበር።
ስለሆነም የከተማችን ነዋሪዎች በሁሉም የሥራ መስኮች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረገና እያደረገ ያለ ሲሆን በተለይም የአዲስ አበባ ሰላም ተጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ ለሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ትልቅ ትልቅ ተምሳሌት ሆኖ ይገኛል። በመሆኑም ሕዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋናና ዕውቅና ሊቸረው ይገባል።
ይሁንና አሁንም በከተማችን የሚስተዋሉና በልዩ ትኩረት ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉ በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ እና ምከር ቤቶችም የክትትል ድጋፍና ቁጥጥር ሥራችን አጠናክረን የተጠያቂነት አሠራር በጥብቅ ዲስፒሊን እየተመራ ተግባራዊ አየተደረገ ይገኛል።
ከምክርቤቱ የምርጫ ዘመንጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም በወሰነው መሠረት እና እንዲሁም ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የከተማውን አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995ን ለማሻሻል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ እና “ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤቱ እና አጠቃላይ የከተማው የአስተዳደሩ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል” በሚል በደነገገውና በወሰነው ውሳኔ መሠረት ህጋዋ ዕውቅና አግኝቶ የቀጠለ አስተዳደር እንደሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሲሆን በዚሁ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 አንቀጽ 3 ስር “ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት አባላት ውስጥ ወይም ከምክር ቤት አባላት ውጭ የሚሾም ሆኖ የሥራ ዘመኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ይሆናል”ተብሎ በግልጽ በተደነገገው መሠረት የከተማው ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት በወቅቱ በተገኙት ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ስለሆነም “የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመት የነዋሪው ውክልና የለውም” ህጋዊ አይደለም በሚል የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሰሰቦች ምንም ዓይነት ህጋዊ መሠረት የሌላቸው እና በስሜት ብቻ የሚንጸባረቁ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የሚፃረር እና ህገወጥ እንደሆነ ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ሊረዳው ይገባል።
ይሁንና አስተዳደሩ በከተማችን ነዋሪ ተሳትፎ ጭምር በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሌት ተቀን ደፋ ቀና በሚልበትና በዕቅድ ተይዘው እየተተገበሩ ያሉ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት እየተረባረበ እና ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ወገኖች በሕግ የተቋቋመውን የአስተዳደሩን ተግባራት በማደናቀፍ የሕዝብ ያልሆኑ ጥያቄዎችን የሕዝብ በማስመሰል ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ስለሆነም በአገራችን ብሎም በከተማችን የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ በቅርቡ በከተማችን ሰላምን ለማደፍረስ እየታዩ ያሉ ኢ-ሕገመንግሥታዊ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተልና ሕገወጥ እንቅስቃሴ አድራጊዎችን በሰላማዊ መንገድ በመታገል የከተማችን ነዋሪዎች እንደወትሮው ሁሉ የከተማችንን ሰላም በማስከበር የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጐን እንደሚቆም ያለንን ጽኑ እምነት እየገለጽን፡-
1ኛ. ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡ፣ በህጋዊ መንገድ በተመረጠው አስተዳደር ላይ አመጽ የሚያነሳሱ ማናቸውም ድርጊቶች ለማንም የማይጠቅም ህገወጥ ድርጊት እና ፀረ-ህገመንግሥትም ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም፤
2ኛ. አሁን ያለው የከተማው አስተዳደር ህጋዊ መሠረት ያለው እና በም/ቤቱ ፀድቆ የተሾሙ በመሆኑ መላው የከተማው ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደር ጐን በመቆም በከተማችን ነዋሪዎች ድምፅ ውክልና የተሰጠውን ም/ቤት ሥልጣን ወደጐን በመተው እየተነሱ ያሉ የማደናገሪያ አስተሳሰቦችን አምርሮ እንዲታገል፤
3ኛ. በከተማችን ውስጥ የላቀ ልማት ለማስመዝገብ፣ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለውጡን ባስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ትብብር እንዲያደርጉ እና ከከተማው አስተዳደር ጐን እንዲቆሙ ጥሪ እያቀረብን፣ የብሄርብሄረሰቦችና ሕዝቦች የቃልኪዳን ሠነድ እና የህጐች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገመንግሥት የማክበር፣ የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን በመወጣት ሕዝቡን በማደናገር የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ ሌት ተቀን የሚጥሩ ኃይሎችን በመታገል ከከተማ አስተዳደሩና ከምክርቤቱ ጐን በመሆን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ፤
4ኛ. የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ ከተማችን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመቻቻል በአብሮነት ለሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ሕዝብ የሚኖርባት የሁላችንም ከተማ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆንዋ ታውቆ ከከተማው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የሕጐች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ምላሽ የሚያገኝ ስለሆነ ፍጸም የግጭት መንስኤ መሆን አይገባውም፤
5ኛ. የከተማው አስተዳደር እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባሻገር እያከናወነ ያላቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞችን አጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን፣ እንደወትሮው ሁሉ የከተማችን ነዋሪዎችም ህግና ሥርዓት እንዲከበርከ አስተዳደሩ፣ ከሕግ እና የፀጥታ አስከባሪ አካላት ጐን በመሆን ለሰላም ዘብ በመቆም የተለመደው ትብብሩን እንዲቀጥል እንጠይቃለን።
እናመሰግናለን!
ወ/ሮ አበበች ነጋሽ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
አዲስ አበባ
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.