የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውን ይህን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ የቤት መግዣ የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች በዚህ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይፋ አደረገ። አገልግሎቱ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ጨምሮ ሌሎች የወለድ አገልግሎትን የማይፈልጉ ዳያስፖራዎችም እንዲጠቀሙበት የተዘጋጀ ነው።
የባንኩ የጥራት ቁጥጥር ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እመቤት መለሰ አዲሱን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ ፋይናንስ አገልግሎት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “ለመኖሪያ ቤት መግዣ የሚውለው ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ ፋይናንስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከቀረቡትና ዳያስፖራውን ከሚመለከቱ የባንክ አገልግሎቶች በተለየ መንገድ ይተገበራል” ብለዋል።
ዳያስፖራው ወዲዓ’ህ የቁጠባ ሒሳብን በመጠቀም ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአሜሪካን ዶላርና በዩሮ መቆጠብ ከቻለ፣ የፋይናንስ ጥያቄውን ለባንኩ በማቅረብ መስተናገድ እንደሚችል ወይዘሮ እመቤት ተናግረዋል።
ግንባታው የተጠናቀቀና ጅምር ቤት ለመግዛት የሚውለው የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ቤት ችግር እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ታስቦ ለዳያስፖራው የተዘጋጀ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ነው። የፋይናንስ አገልግሎቱን መስፈርቶች ማሟላት የሚችሉ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በሚኖሩበት አገር በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርበው የወዲዓ’ህ ቁጠባ ሒሳብ በመክፈት መቆጠብ የሚችሉ ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ቅድመ ክፍያ በአንድ ጊዜ ወይም በተለያዩ ጊዜያት በመቆጠብ መክፈል ይችላሉ። ለቤት መግዣ የሚውለውን ፋይናንስ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ የቆይታ ጊዜ ከፍለው መጨረስ እንዲችሉም ተመቻችቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውን ይህን ከወለድ ነፃ የዳያስፖራ የቤት መግዣ የፋይናንስ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች በዚህ አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ወይዘሮ እመቤት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦