Home › Forums › Semonegna Stories › ከትውልድ ትውልድ በአንድ ሙያ ህዝብን ያገለገሉት ፈንቅር ሳረነ እና ተተኪዎቻቸው
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 8 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 28, 2019 at 6:50 pm #9972SemonegnaKeymaster
በቤተ ጉራጌ ዘንድ በወጌሻ ሕክምና ሙያቸው ስማቸው እጅግ ከፍ ብሎ የሚጠራው አቶ ፈንቅር ሳረነ ሲሆኑ፥ ይህም ሙያ ከእርሳቸው አልፎና ከልጅ ልጆቻቸው ተዋርሶ፣ አሁን የልጅ ልጆቻቸው በቤተ ጉራጌ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያገለገሉ ይገኛሉ። አቶ መኮንን አመርጋ ደግሞ የአቶ ፈንቅር ሳረነ አራተኛ የልጅ ልጅ ናቸው።
ኑሬ ረጋሳ (የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)
ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ከባህላዊ የሕክምና ዘዴዎች ውስጥ የወጌሻ ሕክምና አንዱ ነው። የሰዉ ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች በአካላቸዉ ላይ የተለያዩ አደጋዎች ይገጥማቸዋል። በአንድ ወቅት በወጌሻ ፈንቅር ሳረነ በሰውነታቸው ላይ እባጭ ወጥቶባቸው ሁለተኛ ወገን ባለማግኘታቸው በቻሉት አቅም ራሳቸውን አክመው እባጩን በማዳናቸው ምክንያት አድርገው የጀመሩት የባህላዊ ወጌሻ ሙያ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ አሁንም ድረስ የፈንቅር ሳረነ የልጅ ልጆቻቸው ከቤተ ጉራጌ ክልል አልፈው በሌሎችም ቦታዎች ህብረተሰቡን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ ፈንቅር ሳረነ የተወለዱት በ1814 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ የወግወረ በቢባል አካባቢ ነበር። የአካባቢው ማህበረሰብ አንደግባ የሚል የክብር ስም ሰጥቷቸዋል። በባህላዊ ሕክምና ህዝቡን የማገልገል እሳቤ ይዘው ወደ ወጌሻነት ሙያ የገቡት ፈንቅር ሳረነ ለዘመናት ህዝቡን አገልግለዋል። የወጌሻነ ሕክምና አገልግሎታቸው እና ከተለያዩ እፅዋት በባህላዊ መንገድ በመቀመም የሚያዘጋጇቸው መድኃኒቶች እስከ በጊዜው እስከ ቤተ መንግስት ድረስ አድርሷቸዋል። ፈንቅር ሳረነ የ8 ወንድ ልጆችና የአንድ ሴት ልጅ ወላጅ አባት ሲሆኑ ለአብነት ያህል ካቤ ፈንቅር ሳረነ፣ ጫሚሳ ፈንቅር፣ ድድራ ፈንቅር፣ ገብረማሪያም ፈንቅር፣ እንዱሁም ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ወጌሻ መኮንን አመርጋ የአራተኛ የልጅ ልጅ (ማለትም ፈንቅር፣ መኮንን አመርጋ ጫሚሳ ፈንቅር) ሲሆኑ፥ እሳቸውም በሚሰጡት የወጌሻነት ሕክምና አገልግሎት አንቱታን አትርፈዋል።
ወጌሻ መኮንን አመርጋ እንደሚሉት በባህላዊ ሕክምና ሙያ፣ ልምድና ዕውቀት የቀሰሙት የልጅ ልጅ በሆኑት በወጌሻ ወልዴ ጫሚሳ እንደሆነና ወጌሻ ወልዴ ጫሚሳ ከቤተ ጉራጌ ክልል አልፈው እስከ ስልጢ ድረስ እየዞሩ ያገለግሉ እንደነበረም ተናግረዋል። ድርድራ ፈንቅር ከጅማ እስከ ከፋ ድረስ የባህላዊ ሕክምና ሲሰጥ እንደነበረ እንዲሁም የካቤ ፈንቅር ልጆች (ለምሳሌ ዜናዬ ካቤ፣ መዝገበ ካቤ) አዲስ አበባ ላይ አገልግሎት እንደሰጡ፤ በወሊሶና አካባቢው ደግሞ ተክሌ ሙራረ በአግባቡ የወጌሻነት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ይሰጡ እንደነበረም አስረድተዋል። የልጅ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ ዙሪያሽ ደግሞ አጠቃላይ ቤተ ጉራጌ በአካለለ መልኩ ቸሃ ላይ መቀመጫ አድርገው ይሠሩ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
◌ የEBS ቴለቭዥን አርአያ ሰብ መርሀግብር በፈንቅር ሳረነ የሕይወት ታሪክ ላይ የሠራውን ጥንቅር እዚህ ጋር ይመልከቱ
የወጌሻነት ሙያ ከአጎታቸው የተማሩት መኮንን አመርጋ ወልቂጤ ከተማ ላይ በመምጣት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ወልቂጤና አካባቢዋ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገልገል ተጠቃሽ የሆነው ወጌሻ መኮንን አመርጋ ለበርካታ ዓመታት ቤታቸው ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ የህብረተሰብ ማለትም በስፖርታዊ ውድድሮች ተሰብሮና እግሩ ወልቆ ለሚመጣ፣ የተሸከርካሪ አደጋ ለደረሰበት፣ ውልቃትና መሰል አደጋ ለደረሰበት ሰው አገልግሎት በመስጠት ይታወቃሉ።
ወጌሻ መኮንን አመርጋ የወልቂጤ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ብሔራዊ ሊግ እያለ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያህል በወጌሻነት በማገልገል ለስፖርተኞች ጥሩ ወንድማዊ ፍቅርን በመለገስ በጫወታ ወቅት የሚደርስባቸው ጉዳት በማከም ስፖርተኞች ውጤታማ እንዲሆኑና አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ ሊግ በሙያቸው የበኩላቸውን ሚና ተወጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ዓመታት የወረዳውና የዞን ውድድሮችን እንዲሁም በየዓመቱ በሚደረጉ የትምህርት ቤቶች ውድድሮች ላይ ሳይሰለቹ በቅንነት በማገልገል ስማቸው ከምስጋና ጋር ይነሳል።
ለሙያው እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ባላቸው ክብር የተነሳ በጣም ጉዳት ደርሶበት ውይም ደርሶባት መኖሪያ ቤቱ መምጣት የማይችሉት ጉዳተኞች እስከ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ሙያዊ እገዛ በማድረግ ይታወቃሉ – ወጌሻ መኮንን። አንድ ባለ ጉዳይ አገልግሎቱን ለማግኘት ከመጣ ገንዘብ እንኳን ባይኖረውም መጎዳትና አካለ ስንኩል መሆን የለበትም በማለት አገልግሎቱን በነጻ በመስጠት በጎነታቸው የሚታወቁት መኮንን ዓመርጋ፥ የወጌሻነት ሙያ ወደ ልጆቻቸው ለማስረጽ ሙያውን ሙሉ ለሙሉ እንዲያውቁት ለማድረግ የዕውቀትና የሙያ ሽግግር የማድረግ ዓላማ ይዘውም ይሠራሉ።
በዚህም የበኩር ልጃቸው የአባቱን የወጌሻነት የጥበብ ትምህርት የእረፍት ጊዜውን በመጠቀም አባቱን በማገዝና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት በመቅሰም ወይም ትምህርት በመውሰድ፣ ወጌሻ መኮንን ራቅ ወዳለ ቦታ ከሄዱ አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነና ሙያውን ሙሉ ለሙሉ አውቆ በእረፍት ጊዜው እየሠራበት እንደሆነም ወጌሻ መኮንን ገልጸዋል።
መንግስት የባህላዊ ሕክምናው ዘርፍ ለማዘመን ነጻ የትምህርትና ስልጠና እድል በማመቻቸት የሕክምናውን ሳይንስ እንዲያውቁት በማድረግ ረገድ ውስንነት መኖሩን አስታውቀው፥ የጤናውን ትምህርት ባይወስዱም ህብረተሰቡን እያገለገሉበት ያለውን የወጌሻ ሙያ ዕውቀታቸውን የበለጠ ለማዳበር ቴክኖሎጂ በመጠቀም እና ሀኪም ጓደኞቻቸውን በማማከር ትምህርት እየተማሩ እንደሆነና በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን ውስንነት እየቀረፉ እንደሆነም አስረድተዋል። በሳምንት በርካታ ሕመምተኞች በቀላልና ከባድ አደጋ ቤት ድረስ መጥተው አገልግሎት እንደሚያገኙ የተናገሩት መኮንን ዓመርጋ በከተማው ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት የሚሰጡት በመኖሪያ ቤታቸው ሲሆን መንግስት በከተማው ሴንተር ቦታዎች ላይ ቋሚ መሥሪያ ቦታ ቢያመቻችላቸው የበለጠ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል።
የወጌሻ ሙያ ከጀመሩ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩት መኮንን በሥራ ላይ ብዙ ገጠመኞች እንደገጠማችው አስታውሰው ለአብነት ያህል በአንድ ወቅት በእግር ኳስ ሜዳ ላይ አንድ አጥቂ ጎል ለማግባት ሲል እርስ በእርስ ተጋጭተዉ ላንቃው ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ምላሱን ማንቀሳቀስ አቅቶት ሊሞት ሲል አንደምንም ርብርብ አድርገን አፉን በመክፈት በባንድራ እንጨት አፉን በመክፈት ወደ ሕክምና ማእከል በመውሰድ እንዳዳኑትም ተናግረዋል።
አቶ ኢሳያስ ናስር ቀደም ሲል የወልቂጤ ከነማ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ሲሆ ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ ከሕክምናው ሙያው በተጨማሪ ክለቡን ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋትነት የከፈሉ ምርጥ ባለሙያ ናቸው ብለው ይመስክሩላቸዋል። አክለውም፥ ስፖርተኞች የከፋ አደጋ እንኳን ቢደርስባቸው ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን በመጠቀም የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ጉዳት የደረሰባቸው ሲታደጉ ነው የሚታዩት። ከስፖርተኞች ጋር ጥሩ ፍቅር በማሳየት ከብሔራዊ ሊግ ጀምሮ ክለቡ አሁን ለደረሰበት ሁኔታ የአንበሳውን ሥራ ሰርተዋል፤ አሁንም ድረስ በበጎ ፍቃደኝነት በሙያው አገልግሎት በመስጠት ናቸው በማለት የወጌሻ መኮንን አመርጋ ታታሪነት ይመሰክራሉ። አቶ ኢሳያስ በመቀጠልም የሙያና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ መንግስት እነዚህ የወጌሻ ባለሙያተኞች በተገቢው ምቹ የሥራ ቦታ ቢያመቻችላቸው የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።
አንዳንድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ ቅንና ለሙያው ክብር ሰጥተው የሚሠሩ ባለሙያ እንደሆኑ፣ ሰውን ለማዳን እንጂ ገንዘብ ማትረፍን ዓላማ አድርገው የማይሠሩና አቅም ለሌላቸው በነጻ ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ከህመማቸው እንዲድኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ባለሙያ መሆናቸውን ይመሰክሩላቸዋል። የዚህ ጹሁፍ አዘጋጅም ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ በሙያው ያላቸውን የካበት ልምድ እና ህብተረሰቡን ለማገልገል ያላቸውን ከፍተኛ ፈላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሙያው ያላቸውን መልካም ፍቃድ የበለጠ አጠናክሮ እንዲሰራበትና በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲታደግ እያልኩኝ ወጌሻ መኮንን ዓመርጋ መንግስት በዘርፉ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ የመስሪያ ቦታ እንዲያመቻችለት እና ተተኪ ባለሙያተኞች መፍጠር ይኖርበታል።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.