ዋትስአፕ (WhatsApp) ለስለላ ተግባር ውሎ እንደነበር ተገለጸ

Home Forums Semonegna Stories ዋትስአፕ (WhatsApp) ለስለላ ተግባር ውሎ እንደነበር ተገለጸ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #10851
    Semonegna
    Keymaster

    ዋትስአፕ (WhatsApp) ሰኞ፣ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፥ ጥቃቱ የተመረጡ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን (“select number” of users) ዒላማ ያደረገ ነበር፤ የተቀነባበረውም የላቀ ችሎታ ባላቸው ሀከሮች ነው ተብሏል።

    አዲስ አበባ (ኢመደኤ)– የኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች (ሀከርስ) የዋትስአፕ መተግበሪያን (WhatsApp app) ተጠቅመው ስልኮችና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ላይ መሰለያ ጭነው እንደነበረ ተረጋገጠ።

    መሰለያውን የጫኑት የዋትስአፕ መተግበሪያ ላይ ያለ ክፍተትን ተጠቅመው ነው ተብሏል።

    በዓለም ላይ 2.3 ቢሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ቀዳሚ ማኅበራዊ ሚዲያ (social media) በሆነው ፌስቡክ (Facebook) ስር የሚተዳደረው ዋትስአፕ ይፋ እንዳደረገው፥ ጥቃቱ የተመረጡ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን (“select number” of users) ዒላማ ያደረገ ነበር፤ የተቀነባበረውም የላቀ ችሎታ ባላቸው ሀከሮች ነው ተብሏል።

    የለንደኑ ዓለም አቀፍ ጋዜጣ ፋይናንሽያል ታይምስ እንደዘገበው፥ ጥቃቱ የተሰነዘረው ‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ (NSO Group) በተባለ የእስራኤል የደኅንንት ተቋም ነው። ባለፈው ሀሙስ (ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.) ዋትስአፕ የተፈጠረውን ችግር ማስተካከል ችያለሁ ብሏል።

    ጥቃቱ እንደተሰነዘረ የታወቀው በያዝነው ወር መባቻ ላይ ሲሆን፥ ሰኞ ዕለት (ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም.)  ዋትስአፕ 1.5 ቢሊየን ተጠቃሚዎቹ የተሻሻለውን መተግበሪያ እንዲጭኑ (‘update’ እንዲያደርጉ) ጠይቆ ነበር።

    መሰለያ የጫኑት አካሎች በዋትስአፕ መሰለል ወደሚፈልጉት ግለሰብ ይደውላሉ። ከዛም መሰለያውን ይጭናሉ። ግለሰቡ ስልኩን ባያነሳም እንኳን መሰለያውን ከመጫን አያግዳቸውም ተብሏል። ፋይናንሽያል ታይምስ እንዳለው ከሆነ ጥሪ ያደረገው አካል ማንነት ከደዋዮች ዝርዝር (call log) ይጠፋል።

    ዋትስአፕ ለቢቢሲ እንዳሳወቀው፥ ለመጀመርያ ጊዜ ይህ ክፍተት መፈጠሩን ያስተዋለው የድርጅቱ የደኅንነት ክፍል (security team) ነበር። ወዲያው ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እንዲሁም ለአሜሪካ የፍትህ ቢሮ (Department of Justice) አሳውቀዋል።

    “ጥቃቱ ከግል ድርጅት መሰንዘሩን የሚያሳይ ምልከት አለ። ከመንግሥት ጋር በመሆን ያልተፈለገ የስለላ ሶፍትዌር (spyware) በመጠቀም ስልክ መቆጣጠር የሚያስችል ነው” ሲሉ የዋትስአፕ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙኀን ገልጸዋል።

    ‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ ከመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸው ተቋማት ወንጀልን ለመከታከልና የሽብር ጥቃት እንዳይደርስ ለማድረግ እንዲያውሉት አልሞ የሠራው ነው። ሆኖም አሠራሩ ያላግባብ ጥቅም ላይ ውሎ ከሆነ ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።

    ዋትስአፕ ምን ያህል ሰዎች ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ለማወቅ ጊዜው ገና ነው ብሏል።

    ከዚህ ቀደም በ’ኤንኤስኦ ግሩፕ’ ጥቃት ደርሶብኝ ነበር ያለው የመብት ተከራካሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International)፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መሰል ጥቃት ሊደረስባቸው እንደሚችል ስጋት ነበረን ብሏል።

    የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቴክኖሎጂ ክፍል ዳይሬክተር ዳና ሌግሌተን (Danna Ingleton) እንዳሉት፥ ታዋቂ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን ለመቆጣጠር በመንግሥታት ጥቅም ላይ የሚውል አሠራር ነው።

    የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር የ’ኤንኤስኦ ግሩፕ’ን ፍቃድ እንዲቀማ ለመጠየቅ በአምነስቲ ኢንተተርናሽናል የተመራ የፊርማ ስብስብ ቴል አቪቭ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

    ምንጭ፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ዋትስአፕ


Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.