Home › Forums › Semonegna Stories › ቅምሻ ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ሐሰተኛው (በእምነት ሥም)” መጽሐፍ…
Tagged: ሐሰተኛው, ዓለማየሁ ገላጋይ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
July 24, 2020 at 1:26 pm #15181AnonymousInactive
እነሆ ቅምሻ በቅርቡ በገበያ ላይ ከሚውለው የደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ሐሰተኛው (በእምነት ሥም)” መጽሐፍ…
(ሙሉቀን አስራት)
…
የንውዘት ጥሻዬን ፈራሁት፤ የሚያናጥበኝ ሐሳብ ለማግኘት ወደ ድንኳ መጽሐፍ መደርደሪያዬ ማተርኩ። ሽንጠ መልካሞቹን መጻሕፍት ብቻ ካለሁበት ሆኜ ርዕሳቸውን ለማንበብ ቻልኩ። የመጀመሪያው ተተናኮለኝ። “IDIOT’S” እስካሁን ለባጀሁበት የሀሳብ መናወዝ ምላሽ መሰለኝ። ደደብነቱን ያልተቀበለ ለደደቦች የተዘጋጀ መጽሐፍ ይገዛል? ቀጣዩ “What Good Is God?” እግዚአብሔር ከመጥፎነት የተነጠለ ጥሩነት ይኖረዋል? ይሄንን የማይመስል መነሻ ለማረጋገጥ የሚዳክር ደራሲ የፃፈው ነው። ግማሽ ደርሼ እንዳቆምኩት ትዝ አለኝ። “Before the Beginning” መጽሐፍ የምንምነት “ቅዱስ” መዝገብ ነው። ዘፍጥረት አለው። ከቁስ አካልነት ወደ ህይወት እንዴት ሽግግር እንደተካሄደ በማተት መላምቱን የዕውቀት ረድፍ ውስጥ ለመክተት ይጥራል። ሳይንስ ከተጨባጭነት ወደ ምናባዊነት አፈግፍጓል። በአጭሩ ልቦለድ ሆኗል የሚያስብል ደረጃ ላይ ነው።…
አዎ፣ በወርቅ የተዘመዘመ ድንኳኑን ይተክላል። የድንኳኑ ተራዳና ካስማው ወርቅ ነው አሉ። እሱ ግን ጉፍጫ ነው። ቁመተ መላላ፣ አንገተ ሰላላ፣ ጭንቅላተ ሞላላ፣ ቀኝ አይኑ የተኮላሸች፣ ግራ አይኑ የተቅላላች።…
ትንቢት ይቀደሞ ለነገር እንዳለ ትንቢቱ እየተፈፀመ ነው። ሰውየው ጭንቅላተ ሞላላ፣ አንገተ ሰላላ፣ ቁመተ መላላ፣ አንድ አይኑ የከሰመች፣ ሌላይቱ አይኑ የተቅላላች ናት። ቁርጥ ሐሰተኛ መሲሁን።…
የመጽሐፉ ርዕስ በጉልህ ታየኝ “The Last Temptation of Christ” ይላል። [Nikos] Kazantzakis ደራሲው ነው። በመጨረሻ አልጋ ላይ በፅኑ ህመም ተይዞ ነው አሉ። እግዚአብሔር ፊቱ የቆመ ያህል አይኑን እያንከራተተ ይለምን ነበር። ‘አስር ዓመት ብቻ! አስር ዓመት ስጠኝና ውስጤ ያለውን ከሁሉ የላቀ መጽሐፍ ልገላገል። አስር ዓመት’ እያለ ይማፀን ነበር።“እኛ እንጂ የምናሳዝነው” ተበሳጨሁ እንዴ? “እስኪ የፃፋቸውን መጻሕፍት አስቧቸው? Zorba the Greek? Freedom or Death? Report to Greco?… ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጥ መጽሐፍ ውስጤ አለ እያለ ነበር’ኮ። እሱ በፃፋቸው ምን ተጠቅሞ ነው ባልፃፋቸው የሚጎዳው? ተፈጥሮ በመክሊታቸው ያተረፉና መክሊቶቻቸውን የቀበሩ እያለች የተለያየ የሞት ክፍሎች የምታዘጋጅ ይመስልሃል? የሰው ልጅ ሥራ ምድር ላይ የሚካተት የምድር ላይ ጣጣ ብቻ ነው። የምድር ሥራ የሚሰፍርበት የሰማይ ቤት መዝገብ የለም። አፈራችን ቦንኖ እንዳልሆንን የምንሆን ቁራሽ የትቢያ ጥቢኛ ነን።”
…
…ሐሰተኛው መሲህ የተሰጠው መለኮታዊ ኃይል ምን ይሆን? እንደሙሴ በትር ተሰጥቶታል? ባህር እንዲከፍልበት? ከድንጋይ ላይ ውኃ እንዲፈልቅበት? የፈርኦንን ቃላተኛ በትር የሚውጥ በትር? ወይስ እንደ ዚየስ እና እንደ አቡየ ጣዲቁ ገደል እንደአክርማ የሚሰነጥቁበት መብረቅ?……
መጽሐፍ፦ ሐሰተኛው /በእምነት ሥም/
ደራሲ፦ ዓለማየሁ ገላጋይ
የታተመበት ዓምት፦ 2012 ዓም“ሐሰተኛው /በእምነት ሥም/” ለደራሲው (ዓለማየሁ ገላጋይ) አስራ አራተኛው መጽሐፉ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት፦ ውልብታ፣ አጥቢያ፣ ታለ /በዕውነት ስም/፣ ወሪሳ፣ መለያየት ሞት ነው፣ ቅበላ፣ በፍቅር ስም፣ የፍልስፍና አፅናፍ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት፣ ኢሕአዴግን እከሳለሁ፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ኩርቢት፣ መልክአ ስብሐት፣ የሚባሉ መጽሐፍትን ጽፎ ለአንባብያን አቤርክቷል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.