ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ልዑካን ቡድን አባላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲካሄድ የቆየው መንግስት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለውን ዝግጁነት የሚለይና ለችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ አውደ-ጥናት ተጠናቀቀ።
በአውደ ጥናቱ የመንግስት አግልግሎት አሰጣጥ፣ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት፣ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ክፍተት ተለይተውበታል – ሚኒስቴሩ እንደዘገበው።
የጤና አስተዳደር፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት፣ የመረጃ ግንኙነት (ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን) ቴክኖሎጂ ደኅንነት፣ በባንክ አገልግሎት፣ በኢንሹራንስ አገልግሎት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኦዲት አገልግሎት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ የውሃ አወጋገድ ላይ ክፍተቶች ተለይተዋል።
አሜሪካ ውስጥ ቨርጂንያ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Virginia International University; Fairfax, VA) መምህር በሆኑት ዶ/ር ተፈራ በየነ የተመራው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ልዑክ ክፍተቶቹን ከለዩ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
◌ ከ7ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በመላው አገሪቱ ሊቋቋሙ ነው
ባለሙያዎቹ በኢንሹራንስ፣ በህክምና ቴክኖሎጂ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአሜሪካን ሀገር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ከቡድኑ ጋር ለ1 ሳምንት ክፍተቶችን እና ጉድለቶችን የመለየት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በየዘርፉ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን በኃላፊነት ወስደው ወደ ተግባር የመቀየር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በማጠቃለያው ላይ፥ ልዑካኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወይም የሚመለከተው መንግስታዊ ተቋም ዕድሉን ከሰጠን የሀገራችንን ችግር ለመፍታት በቂ አቅም አለን ብለዋል። ወደፊትም በማንኛውም መልኩ ሀገራቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እና ጀማል በከር ልዑካኑ ሀገራቸውን ለመረዳት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል።
የልዑካን ቡድኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተክተሎ የመጡ ናቸው።
ምንጭ፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ