Home › Forums › Semonegna Stories › ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
Tagged: ቂሊንጦ, ብሔራዊ ባንክ, ኤርሚያስ አመልጋ, ዘመን ባንክ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 11 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 17, 2019 at 10:01 am #9744SemonegnaKeymaster
ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ – (ኤርሚያስ አመልጋ – ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት)
(አጽንቼ ያቆምኩትን ባለውለታውን ዞሮ የወጋው ዘመን ባንክ)ከ20 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሼ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ስሥራ እንደመቆየቴ፣ የሥራዬ ባህሪ ከባንኮች ጋር ያገናኘኝ ነበርና አዘውትሬ ወደተለያዩ የአገሪቱ ባንኮች እሄድ ነበር። ሁሉም ባንኮች ግን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የማይጠቀምና የደንበኞችን ፍላጐት በተቀላጠፈ መልኩ የማያረካ፣ ኋላቀር የባንክ አሠራር ይዘው ነበር የማገኛቸው።
በ2001 ዓ.ም. በባንኩ ዘርፍ ላይ ጥናት ካደረግኩ በኋላ፣ በወቅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ባንኮች የሚታየውን ኋላቀር የባንክ አሠራር ወደ ጐን በመተው፣ ለአገሪቱ አዲስ የሆነና ባደጉት አገራት የሚሠራበት ዘመናዊ አሠራር የሚከተል በአይነቱ የተለየ ባንክ ለማቋቋም ወሰንኩ።
የማቋቁመው ባንክ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የነበሩ ባንኮች ከሚሰጡት የተለየ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር የሚከተል እንዲሆን በማሰብም፣ አቅም ላላቸው ደንበኞች ብቻ ትኩረት በመስጠት፣ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ባልተለመደ መልኩ በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት አዲስ የባንክ አሠራር ቀየስኩ። ባንኩ በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም፣ የባንኩ ባለሙያዎች ደምበኞች ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደው የሚያገለግሉበትና ተደራሽነት ያለው አዲስ አሠራር እንዲኖር በማድረግ አገልግሎቱ በቅርንጫፍ እጥረት እንዳይስተጓጎል ተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘዴዎችን ተግባራዊ አደረግኩ።
◌ ዘመን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.1 ቢልዮን ብር ማትረፉንና ይህም ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15.3 መቶ ብልጫ እንዳለው አስታወቀ
ወደ አክሲዮን ሽያጭና ባንኩን ወደማቋቋም ገባሁ። የአክሲዮን ሽያጩን በአግባቡ ለማከናወንና የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ ለመሰብሰብ የባንኩን አጠቃላይ አደረጃጀት፣ የአገልገሎት አሰጣጥና የሥራ ዕቅድ በተመለከተ ለባለሃብቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በተደጋጋሚ በማዘጋጀት ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት በከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት ከ3 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ባለአክሲዮኖች 150 ሚሊዮን ብር ያህል አሰባሰብኩ።
ዘመን ባንክን ለማቋቋም የጀመርኩት ጥረት በተለይ በብሔራዊ ባንክ ተደጋጋሚ እንቅፋቶች ገጥመውት ነበር። ያም ሆኖ ግን፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት ፈተናዎችን ሁሉ ለማለፍ ተጋሁ። ከእልህ አስጨራሽ ቢሮክራሲና ኢፍትሃዊ ጣልቃገብነት በኋላም፣ ተሳካልኝና ዘመን ባንክን ወደ ሥራ አስገባሁት።
ዘመን ባንክ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሱን አዎታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ ስኬታማ ባንክ ለመሆን ቻለ። ይዟቸው በመጣቸው አዳዲስ የባንክ አሠራሮች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመን ባንክ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው የብዙዎችን ቀልብ መሳብና በርካታ ደንበኖችን ማፍራት እንዲሁም ትርፋማ መሆን የቻለው። ለረጅም አመታት አገልግሎት በመስጠት ከሚታወቁት ሌሎች ነባር ባንኮች ተርታ ለመሰለፍ ጊዜ አልወሰደበትም። በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ በዓመት ከታክስ ውጭ 120 ሚሊዮን ብር አትርፏል። ዘመን ባንክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጐናፀፈው ተጨባጭ ስኬት ብዙዎችን ማስገረሙን ቀጥሏል።
ዘመን ባንክ በተቋቋመ በሦስተኛው ዓመት…
በዘመን ባንክ የመመሥረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ ላይ፣ ከባንኩ ዘጠኝ የቦርድ አባላት መካከል ስድስቱ በየሶስት አመቱ መቀየር እንዳለባቸው በግልጽ ተቀምጧል። በዚህም መሰረት በሦስተኛው ዓመት ላይ፣ ከነባር የቦርድ አባላት ስድስቱን ለመቀየር ዝግጅት ማድረግ ጀመርን። እኔም የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆኔ፣ መቀየር አለባቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ስድስት የቦርዱ አባላት መርጬ፣ ደንቡና አሠራሩ በሚፈቅደው መሰረት ለባለአክስዮኖች እንዲያጸድቁት አቀረብኩ። የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤም፣ ግለሰቦቹ ከቦርድ አባልነታቸው እንዲነሱ ወሰኑ።
◌ ብርሃን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 410 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ይሄን ተከትሎ ነው ነገር መበላሸት የጀመረው። በእኔ ጠቋሚነት ከቦርድ አባልነታቸው ከተነሱት ስድስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ከአባልነታቸው በመነሳታቸው እጅግ በጣም ተበሳጩ። ከእነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪ ለችግሩ መፈጠርና መባባስ መሪ ተዋናይ የሆነ አንድ ልዩ ቂም ያለውና የ500 ሺህ ብር አክሲዮን የገዛ ባለአክሲዮንና ተወካዩ ተጨመሩበት። ይህ ግለሰብ በዘመን ባንክ የምስረታ ዘመን፣ የግሉን ህንጻ እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለባንኩ ለማከራየትና 36 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ ወደ ኪሱ ሊያስገባ ሲሞክር፣ ዕቅዱን ስላከሸፍኩበት ቂም ይዞ ሊያጠቃኝ ደፋ ቀና ሲልና ባንኩን ሲበጠብጥ የኖረ ሰው ነው። ሌሎቹ ሁለቱም፣ በባንኩ የቦርድ አባልነታቸው የሚያገኙትን ጥቅማጥቅም በማጣታቸው ክፉኛ የተናደዱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በባንኩ ምስረታ ወቅት ስለተፈጸሙ ነገሮች የሚያውቁትን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው ሊያጠቁኝ የተዘጋጁት።
ነገሩ እንዲህ ነው…
በአገሪቱ ሕግ መሰረት፣ አንድን ባንክ ለማቋቋም ከባለአክሲዮኖች የሚሰበሰበው ገንዘብ በቀጥታ በዝግ የባንክ አካውንት ውስጥ ነው የሚቀመጠው። የተሰበሰበውን ገንዘብ ማንቀሳቀስና ባንኩን ለማደራጀት በሚያስፈልጉ ሥራዎች ላይ ማዋል የሚቻለው፣ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከሰጠ በኋላ ብቻ ነው። ፈቃድ እስኪሰጥ ድረስ ምንም መሥራት አይቻልም። ገንዘቡ እስኪለቀቅ ጠብቆ መደበኛ የባንክ ሥራ ለመጀመር ደግሞ፣ ቢያንስ ተጨማሪ የሁለት ዓመት ጊዜ ይፈጃል። እኔ ግን ብሔራዊ ባንክ ለዘመን ባንክ ፈቃድ እስኪሰጥና በዝግ ሂሳብ የተጠራቀመው የባንኩ ገንዘብ እስከሚለቀቅ ድረስ ሥራዎች እንዲጓተቱ አልፈለግኩም። በመሆኑም ለባንኩ ምስረታው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከራሴ ገንዘብ ለመሸፈን ወስኜ፣ አርባ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ከራሴ ወጪ በማድረግ፣ አጠቃላይ ባንኩን በቁሳቁስና በሰው ሃይል የማደራጀት ሥራ ሠራሁ። ብሔራዊ ባንክ ብዙ ጊዜ ፈጅቶ ፈቃድ በሰጠን በቀናት ውስጥ ነበር፣ ዘመን ባንክን በቀጥታ ወደ ሥራ ያስገባሁት። ይህን በማድረጌም የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖች ሌላ የማንም ባንክ ባለአክሲዮን ያላገኘውን የሁለት ዓመት ትርፍ ጥቅም አስገኝቻለሁ።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በቅን ልቦና ተነሳስቼ በዘመን ባንክ ምስረታ ወቅት የራሴን ገንዘብ እያወጣሁ ሥራዎችን ስሠራ እንደነበር የሚያውቁትና በእኔ ጠቋሚነትና በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ከቦርድ አባልነታቸው የተሰናበቱት ግለሰቦች እና ተባባሪያቸው ከአመታት በኋላ ይህን ሁኔታ መሰረት አድርገው የግሌን ጥቅም ለማሳደድ ያደረግኩት ነገር አስመስለው ብሔራዊ ባንክ ሄደው በመክሰስ ሊበቀሉኝ ወሰኑ። በባንኩ ምስረታ ወቅት ህጋዊ አካሄድን ባልተከተለ መልኩ የተለያዩ ሥራዎችን ስሠራ እንደነበርና በሕግ ልጠየቅ እንደሚገባ ለብሔራዊ ባንክ አመለከቱ።
◌ ወጋገን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አንድ ቢልዮን ብር ማትረፉንና ይህም ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ49 መቶ ብልጫ እንዳለው አስታወቀ
‘አቶ ኤርሚያስ ዘመን ባንክን ሲያቋቁም የግል ገንዘቡን ተጠቅሟል። የተለያዩ የባንኩ ሥራዎችን ያሠራ የነበረው ጨረታ ሳያወጣና የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ነበር። የአክሰስ ካፒታልም የዘመን ባንክም ሃላፊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም፣ የጥቅም ግጭት የሚያስከትል አሠራር ይከተል ነበር ወዘተ…’ የሚሉ ውንጀላዎችን በዝርዝር በመግለጽ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድብኝ የሚጠይቅ ማመልከቻ ለብሔራዊ ባንክ አስገቡ።
የግለሰቦቹ አቤቱታ ለብሔራዊ ባንክ ትልቅ አጋጣሚ ሆነለት። ዱሮም በሄድኩበት ሁሉ እየተከተለ እንቅፋት ሲፈጥርብኝ የኖረውና እንቅስቃሴዬን ለመግታት ሰበብ ሲፈልግ የነበረው ብሔራዊ ባንክ፣ የግለሰቦቹን ማመልከቻ በደስታ ነበር የተቀበለው። ይህን ተከትሎም፣ መጋቢት 6 ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በዘመን ባንክ የምስረታ ወቅት አንዳንድ ወጪዎች የተደረጉት የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ እንደነበር የሚጠቁሙ ምልክቶች ስለተገኙ በወቅቱ የተደረጉ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በባንኩ በሚሾም ኦዲተር እንዲመረመር መወሰኑን ገለጸ። ይህም ብቻ አይደለም፤ ጉዳዩ ተጣርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስም፣ እኔን ከዘመን ባንክ የቦርድ አባልነቴ በጊዚያዊነት እንዳገደኝ አሳወቀኝ።
ብሔራዊ ባንክ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የተጀመረውና አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶ የተጠናቀቀው የኦዲት ምርመራ ሪፖርት ግን፣ በዘመን ባንክ ምስረታ ወቅት ያከናወንኩት ሥራ እንደተባለው የጥቅም ግጭት የሚያስከትል እንዳልነበር አረጋገጠ። የግል ገንዘቤን ወጪ አድርጌ ባንኩን ሳቋቁም፣ የግሌን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ያከናወንኩትና በሕግ የሚያስጠይቀኝ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሠራሁ መሰከረ።
◌ ደቡብ ግሎባል ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 142 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
የኦዲት ሪፖርቱ በባንኩ ምስረታ ወቅት ተጠያቂ የሚያደርገኝ ህገወጥ ተግባር እንዳልፈጸምኩ ቢያረጋግጥልኝም፣ ብሄራዊ ባንክ ግን ከዘመን ባንክ አመራርነቴ በጊዚያዊነት እንድነሳ የጣለብኝን እገዳ ሊያነሳልኝ አልፈቀደም። የግለሰቦችን ውንጀላ መሰረት አድርጎ የወሰደብኝ እርምጃ አግባብነት የሌለው መሆኑን የሚያሳይና በአፋጣኝ ወደ ሥራዬ እንድመለስ የሚጠይቅና “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚል ርዕስ ያለው ጽሁፍ አዘጋጅቼ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ አወጣሁ። ጽሁፉ በጋዜጣው ላይ በወጣ በሁለተኛው ቀን ግን፣ ከዘመን ባንክ አመራርነት ብቻም ሳይሆን ከማንኛውም የአገሪቱ ባንክ የቦርድ አባልነት እስከመጨረሻው መታገዴን የሚገልጽ ደብዳቤ ከብሔራዊ ባንክ ደረሰኝ።
40 ሚሊዮን ብር ያህል ገንዘብ ከግሌ ወጪ አድርጌ ባንኩን በማቋቋሜ፣ ወንጀል ሠራህ ተባልኩ። የሠራሁት ወንጀል መኖሩ በገለልተኛ አካል በኦዲት እንዲጣራ ተደረገ፣ የኦዲት ምርመራው ውጤት ወንጀል አለመሥራቴን አረጋገጠ። ብሔራዊ ባንክ ግን፣ ወንጀል አለመሥራቴን ቢያረጋግጥም እኔን ከመቅጣት ወደኋላ አላለም። ራሱ ከሳሽ ራሱ ፈራጅ የሆነውን፣ ባለሙሉ ስልጣኑን ብሔራዊ ባንክ በፍርድ ቤት ለመክሰስና መብትን ለማስከበር ህጉ አይፈቅድልኝም። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክን ከስሼ መብቴን ለማስከበር ከመሞከር ይልቅ፣ የደረሰብኝን ግልጽ በደል ለመንግስት ማሳወቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ። የተፈጠረውን ነገር በሙሉ በዝርዝር ገልጬ፣ አቤቱታዬን በደብዳቤ መልክ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላክሁ።
ደብዳቤውን ከላክሁ ከቀናት በኋላ፣ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የመንግስት ተቋማት ድጋፍና ክትትል ሃላፊ የነበሩ ግለሰብ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ሊያወያዩኝ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ወደቢሯቸው አስጠሩኝ። ደስተኛ ሆኜ ወደቢሯቸው ሄድኩ። ጉዳዩን ከስር መሰረቱ አብራራሁላቸው፤ ዘመን ባንክን ለመመስረት ካሰብኩበት ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ የፈጠረብኝን ችግሮች፣ ያደረሰብኝን በደልና በተደጋጋሚ ያስተላለፈብኝን ኢፍትሃዊ ውሳኔዎች በዝርዝር አቀረብኩላቸው። ከሰውዬው ጋር ሰዓታትን የፈጀ ውይይት ካደረግኩ በኋላ ግን፣ ፍትህን ፍለጋ ወደቢሯቸው መምጣቴ ከንቱ ድካም መሆኑን የሚያሳይ ምላሽ ሰጡኝ።
“አቶ ኤርሚያስ በሆነው ነገር ሁሉ እናዝናለን። አንተን ለማጥቃት ተብሎ የተደረገ ነገር የለም። አንተ የምትሠራቸው ሥራዎች ለአገር ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳላቸውና ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ እናውቃለን። አንተ ተራ ነጋዴ እንዳልሆንክም እናውቃለን። ተቋማትን ነው የምትገነባው። ሥራዎችህን እና ጥረትህንም እንደግፋለን። ያው እንደምታውቀው ግን፤ ታዳጊ አገር ውስጥ ነው ያለነው። አንዳንዴ መሆን የሌለባቸው ነገሮች ይሆናሉ። በአንተ ላይ የተፈጸመው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ይገባናል። ችግሩ በጊዜ ሂደት ይፈታል ብለን እናምናለን። ስሜትህ ሳይነካ፣ ጠንክረህ ሥራህን እንድትቀጥል ነው የምንፈልገው። ከዚህ ውጭ ግን፣ በብሔራዊ ባንክ ስልጣንና ሃላፊነት ውስጥ ጣልቃ ገብተን አስተያየት ለመስጠትም ሆነ ውሳኔውን ለማስቀየር ይከብደናል” የሚል ምላሽ ሰጡኝ።
◌ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 658.7 ሚልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍዬ ካቋቋምኩትና ወደትርፋማነት ካሸጋገርኩት ዘመን ባንክም ሆነ፣ አዳዲስ አሠራሮችን አስተዋውቄ ተጨባጭ ለውጥ ከፈጠርኩበት የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ በዚህ መልኩ ያለአግባብ ተገፍቼ እንድወጣ ተደረግኩ። ከዘመን ባንክ አመራርነቴም ከባንኩ ዘርፍም እንድወጣ የተላለፈብኝ ውሳኔ ቢያሳዝነኝም፣ ሌላ የተሻለ ሥራ እንደምጀምርና ነባር ሥራዎችን አጠናክሬ እንደምቀጥል ስለማውቅ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም – ፊቴን ወደሌሎች ሥራዎች አዞርኩ።
በዘመን ባንክ መሥራችነቴ ማግኘት የሚገባኝን ጥቅም አለማግኘቴን ያስታወስኩት እንኳን፣ ባንኩ ሥራ በጀመረ በሶስተኛው ዓመት ላይ ነበር። በዘመን ባንክ የመመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 7 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ የባንኩ መሥራቾችና አደራጆች በመጀመሪያዎቹ 3 አመታት ባንኩ ከሚያገኘው የተጣራ ትርፍ 10 በመቶ የመሥራችነትና የአደራጅነት ጥቅም ያገኛሉ። እኔም የባንኩ መሥራች እንደመሆኔ ከሶስቱ አመታት ትርፍ ይህን ድርሻ ማግኘት ይገባኝ ነበር። በወቅቱ ዋነኛ ትኩረቴ የነበረው ባንኩን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንጂ የግል ገንዘብ በማሳደድ ላይ ስላልነበር፣ ከመጀመሪያውም ሆነ ከሁለተኛው ዓመት የባንኩ ትርፍ ላይ የመሥራችነት ድርሻዬን ተከታትዬ አልተቀበልኩም። ሶስተኛው ዓመት ላይ ግን፣ ቢያንስ ያለፉትን ሁለት አመታት የመሥራችነት የትርፍ ድርሻ አስልቶ እንዲከፍለኝ ለባንኩ ጥያቄ አቀረብኩ።
ዘመን ባንክ በ2002 ዓ/ም በ2003 ዓ/ም በድምሩ ብር 92,634,690.00 /ዘጠኛ ሁለት ሚሊዩን ስድስት መቶ ሰላሳ አራት ሺ ስድስት መቶ ዘጠና/ ማትረፉ በውጭ ኦዲተሮች በተረጋገጠው መሰረት፣ የዚህ ገንዘብ አስር በመቶ እና የውጭ ኦዲተሮች ባንኩ ማትረፉን ካረጋገጡበት ቀን ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ መቶ ወለድ ጋር በድምሩ 10,359,105.69 /አስር ሚሊዩን ሶስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሺ አንድ መቶ አምስት ብር ከ69/100/ እንዲከፈለኝ ነበር የጠየቅኩት። የወቅቱ የዘመን ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ፣ ይህ ክፍያ እንዲፈጸምልኝ ወሰነ። የሚገርመው ነገር ግን፣ አሁንም የብሔራዊ ባንክ ኢፍትሃዊ በደል አልቀረልኝም። ብሔራዊ ባንክ ለኤርሚያስ ይከፈል ያላችሁትን ክፍያ አልቀበለውም፤ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤና የቦርድ ውሳኔ የተላለፈበትን ቃለ-ጉባኤም አላጸድቅም አለ። ዘመን ባንክም ይህን የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ መሰረት በማድረግ ክፍያውን እንደማይፈጽምልኝ አስታወቀኝ።
እዚህ ላይ ዝም ማለት አልፈለግኩም። ዘመን ባንክን በፍርድ ቤት ለመክሰስና በመሥራችነቴ ማግኘት የሚገባኝን ክፍያ በሕግ ለማግኘት ወስኜ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሰረትኩ። የከፍተኘው ፍርድ ቤት ግን ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ/ም ክሱን ውድቅ አደረገው። ይህን ውሳኔ በመቃዎም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቅኩ። ፍርድ ቤቱም የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር የሚገባኝ ገንዘብ እንዲከፈለኝ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ/ም ወሰነልኝ። ዘመን ባንክ በዚህ ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርብም፣ ፍርድ ቤቱ ግን የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለም ሲል ውድቅ አደረገው።
◌ ዳሽን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.14 ቢልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
በፍርዱ መሰረት ክፍያው እንዲፈጸምልኝ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአፈጻጸም አቤቱታ ባቀረብኩት መሰረት ባንኩ ክፍያውን እንዲፈጽም ሲጠየቅ ግን፣ ክፍያውን ሊፈጽምልኝ አልፈለገም። ይልቁንም የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደረና ሌሎች የጥቅም ግጭት ጥያቄዎችን እያነሳ፣ አዳዲስ ክርክሮችን መፍጠሩን ተያያዘው። አልፎ ተርፎም በእኔ ላይ አዲስ የወንጀል ክስ በመመስረት የተወሰነው ገንዘብ እንዲታገድና እንዳይከፈለኝ አደረገ። ባንኩ የመሰረተብኝ አዲሱ ክስ አሁንም ተጨማሪ የጥቅም ግጭት ነበረ የሚል ክስ ነበር። የቀረበብኝ ክስ የወንጀል ክስ መሆኑ ደግሞ እጅግ በጣም የሚገርምም የሚያሳዝንም ነበር።
የራሴን ገንዘብ አውጥቼ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍዬ፣ ብዙ ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን አልፌ ያቋቋምኩትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ ያደረግኩት ዘመን ባንክ፣ ለውለታዬ እውቅና መስጠትና ስሜን በክብር ማውሳት ባይሆንለት የሚገባኝን ጥቅም ለመከልከል በእኔ ላይ ያልተገባ ክስ መመስረቱ በእጅጉ አሳዝኖኛል።
የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለዘመናት ከኖረበት ኋላቀር አሠራር ተላቅቆ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሠራር እንዲዘረጋ በማስቻል ረገድ ፈር ቀዳጅ ሥራ ሰርቻለሁ። ለዘመን ባንክ እዚህ ደረጃ መድረስ ቁልፍ ሚና ተጫውቻለሁ። ገንዘቤን፣ እውቀቴንና ልምዴን ሳልሰስት በመገበር፣ ባንኩንም ባለአክሲዮኖችንም በተለየ ሁኔታ ትርፋማ አድርጊያለሁ። የባንኩ ኢንዱስትሪ ተዋንያንም ሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ውለታዬን ሲዘክሩት ይኖራሉ። የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖችም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሠራሁት ሥራ እውቅና ሲሰጡኝ ኖረዋል። በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ ያጋጠመኝ ድንገተኛ ነገር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
አንድ ማለዳ ከወዳጄ ጋር ወደነበረኝ ቀጠሮ እየሄድኩ እያለ፣ መንገድ ላይ አንድ የማላውቀው ሰው ስሜን ጠርቶ አስቆመኝ። ሰላምታ እንኳን ሳይሰጠኝ፣ በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አቀፈኝ። በግለሰቡ ድርጊት እየተገረምኩ እያለ፣ በስሜት ተውጦ ምክንያቱን ነገረኝ። ‘አቶ ኤርሚያስ… አንተ አታውቀኝም፤ ከአመታት በፊት ዘመን ባንክን ስታቋቁም ተገናኝተን ነበር። ስለምታቋቁመው ባንክ ማብራሪያ ስትሰጥ ሰምቼ፣ ባንኩ አትራፊ እንደሚሆን በመተማመን በ50 ሺህ ብር አክሲዮን ገዛሁ። ያኔ በ50ሺ ብር የገዛኋት የዘመን ባንክ አክሲዮን፣ ዛሬ ሚሊዬነር አድርጋኛለች… አንተ ባታውቀኝም፣ ባለሃብት ያደረግከኝ ባለውለታዬ ነህ! …’ እያለ ደጋግሞ አመሰገነኝ። ከዘመን ባንክ ያተረፍኩት ነገር፣ በሄድኩበት ሁሉ የሚያጋጥመኝ ይህን መሰሉ የሰዎች ፍቅርና አድናቆት ነው።
◌ አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.96 ቢልዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ
ለአመታት ብዙ ነገር የከፈልኩለት ዘመን ባንክ ግን፣ የከፈልኩለትን መስዋዕትነት ከንቱ ሊያስቀረውና የሚገባኝን ጥቅም ሊያሳጣኝ አሁንም ቆርጦ ቆሟል። ወርቅ ያበረከትኩለት ዘመን ባንክ፣ ጠጠር ሊመልስልኝ ደፍሯል። በቅንነት የፈጸምኩትን ተግባር የግል ጥቅሜን ለማሳደድ ያደረግኩት ዝርፊያ በማስመሰል፣ ያለሥራዬ የወንጀል ክስ መስርቶብኛል። ከአገር እንዳልወጣ ሳይቀር አሳግዶኛል። ፍርድ ቤት የዘመን ባንክን መሰረተቢስ ክስ ተቀብሎ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ ዘመን ባንክ ግን ትልቅ ክህደት እንደፈጸመብኝ ህዝቡ ሊያውቀው ይገባል።
ዘመን ባንክ የፈጸመብኝን ክህደት በአደባባይ ላወጣው የወሰንኩት፣ የሚገባኝን ጥቅም አለማግኘቴ አንገብግቦኝ አይደለም። የእኔ ጥያቄ የገንዘብ አይደለም – የፍትህ እንጂ። ህይወቴ በዘመን ባንክ 10 ሚሊዮን ብር የታጠረች አይደለችም። እጄ ላይ ያሉት ጅምር ሥራዎችና የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ፣ ከዘመን ባንክና ከነፈገኝ 10 ሚሊዮን ብር ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። ሰበብ እየፈለገ ሲያስረኝና ሲፈታኝ የኖረው መንግስት፣ ባልተሳተፍኩበት አስቂኝ የሙስና ወንጀል እጄን ይዞ ወደ ቂሊንጦ ላከኝ እንጂ፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚከወንና ለአገሪቱ አዲስ የሆነ ግዙፍ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ወደ አገሪቱ ለማስገባት መንገድ ላይ ነኝ።
በስተመጨረሻም፣ መላው ህዝብ ዘመን ባንክ በእኔ ላይ የሠራውን ግፍና በደል እንዲያውቅልኝ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥሪዬን እያስተላለፍኩ፤ ባንኩ የመሰረተብኝን ሃሰተኛ የወንጀል ክስ አንስቶ የሚገባኝን የመሥራችነት መብት እንዲያከብርልኝ ለማስቻል በማደርገው ጥረት ውስጥ ሁሉም ከጎኔ እንዲቆም እጠይቃለሁ!
ከከበረ ሰላምታ ጋር።
ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ
(የዘመን ባንክ መሥራችና የቀድሞ የቦርድ ሊቀመንበር)
የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም.
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
አዲስ አበባ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.