አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በመናበብ እና አቅማቸውን ይበልጥ አጠናክረው መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከየካቲት 18 እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ተካሂዷል።
የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው ዋና ዓላማ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰብ ጤናን ከማስጠበቅ አንጻር የተሠሩትን በርካታ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ከዕቅድ አኳያ ምን ያክሉን ማሳካት እንደተቻለ፥ በመቀጠልም የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻሉ ዘዴዎችን በመቀየስ ችግሮቹን ለማስወገድ ታስቦ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነበር።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት አጠቃላይ የሕብረተሰቡን ጤና አደጋዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር ሰንሰለቱን ጠብቆ ጠንካራ የሆነ መስተጋብር ሊፈጥር ይገባል፤ በመሆኑም የክልል ጤና ቢሮዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጤናው ዘርፍ በቅንጅት እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፥ ይህ መድረክ በዚህ የግማሽ ዓመት የሕብረተሰቡን ጤና ችግሮች ከመፍታት አንጻር የታዩ ጠንካራ ሥራዎች እና ድክመቶችን በመለየት በቀጣይ ለሚሠሩ ተግባራት ላይ የጋራ መግባባት የሚደረስበት በመድረክ ነው ብለዋል።
ዶ/ር በየነ ሞገስ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደሀገር ከሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር አንጻር እየሠራን ነው፣ ምን ላይስ እንገኛለን፣ በዚህ ግማሽ ዓመት ምን ዋና ዋና ውጤቶች ተመዝግበዋል የሚሉትን በመፈተሽ በቀጣይ ችግር ፈቺ የሆኑ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የጋራ መግባባት የሚደረስበት መድረክ ነው የተዘጋጀው ሲሉ ተናግረዋል።
የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ከዕቅድ አንጻር በግማሽ ዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት፣ በመቶ ቀናት ውስጥ የታቀዱ ተግባራት፣ የነበሩ ጠንካራና አፈፃፀሞችና የነበሩ ክፍተቶች እንዲሁም የነበሩ ስጋቶች፣ ተይዞ የነበረው የበጀት አፈጻጸም፣ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ በሽታዎች ከዕቅድ አንጻር ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ ሀገራዊ የጤና ደህንነት እቅድ፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስጋቶች፣ ተጋላጭነትና ምላሽ ዳሰሳ ጥናት በግምገማ መድረኩ ላይ በዝርዝርና በስፋት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች፣ የኢንስቲትዩቱ የበላይ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የሥራ ሂደት ኃላፊዎች፣ የዕቅድ ክትትል እና ምዘና ኃላፊዎች እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ቡድን መሪዎች በውይይትና ግምገማ መድረኩ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት / ሰሞነኛ ኢትዮጵ