የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከመጪው ህዳር ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል

Home Forums Semonegna Stories የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከመጪው ህዳር ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • Author
    Posts
  • #8383
    Semonegna
    Keymaster

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ እንደሚሰጥ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    አዲስ አበባ (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር) – ከመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክትባቱ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ይሰጣል። የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ በትግራይና ኦሮሚያ በተመረጡ ወረዳዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል።

    በሚኒስቴሩ የክትባት ባለሙያ አቶ ጌትነት ባየ እንዳሉት፥ ክትባቱን ለማስጀመር በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል።

    “ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ መሰጠት ይጀምራል” ብለዋል አቶ ጌትነት ።

    የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መሰጠት ያለበት ከ9 ዓመት ጀምሮ ላሉ ልጃገረዶች ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው ክትባት እጥረት ምክንያት ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ብቻ ነው የሚሰጠው።

    የማህፀን በር ካንሰር መንስኤው “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ” (Human papillomavirus) በሚባል ኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን፥ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደሚያስታውቀው አግባብ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with normal immune systems) በቫይረሱ ከተጠቁ በኋላ የማህፀን በር ካንሰር ምልክት ሳይታይባቸው ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ፣ ደካማ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሴቶች (women with weak immune systems) ደግሞ ምልክቱ ሳይታይባቸው ከ5 እስከ 10 ዓመታት ሊቆዩ እንደሚችሉ ያትታል።

    ለበሽታው ከሚያጋልጡት ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ልጃገረዶች በለጋነት እድሜያቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመርና ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ሲሆኑ፥ ሲጋራ ማጨስም ሌላው ምክንያት ነው።

    ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እና ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ይመከራል።

    በታዳጊ ሀገራት የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ላይ እጅግ በብዛት ከሚታይባቸው ሀያ አገራት ውስጥ አስራ ዘጠኙ የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

    HPV Information Centre የሚባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በሀምሌ ወር በ2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ 7,095 ሴቶች ማህፀን በር ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ በየዓመቱም 4,732 ሴቶች በዚሁ ካንሰር ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ ዘግቧል።

    ምንጭ፦ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እና የዓለም የካንሰር ምርምር ፈንድ (WCRF)

    የማህፀን በር ካንሰር

    #9766
    Anonymous
    Inactive

    የሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠት ተጀመረ
    —–

    ሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት አስራ ሶስት ወር ለሞላቸው ህፃናት በዛሬው እለት በሀገር አቀፍ ደረጃ መስጠት ተጀምሯል።

    የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

    ዛሬ የተጀመረውና ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠው የኩፍኝ በሽታ የመከላከያ ክትባት ህፃናት በሽታውን የመከላከል አቅማቸው እንዲጨምር ብሎም በሌላ በሽታ እንዳይያዙ እና ጤነኛ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

    ከዚህ ባለፈም የኩፍኝ በሽታን ሙሉ በሙሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማጥፋት የተያዘውን ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ የክትባት መርሀ ግብሩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

    የኩፍኝ በሽታ ህፃናትን ለሞት የሚዳርግ ብሎም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚያደርስ በሽታ መሆኑ ይታወቃል።

    በመሆኑም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ህፃናት እድሜያቸው አንድ ዓመት ከ3 ወር ሲሞላቸው ጀምሮ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ የኩፍኝ ክትባቱን በማስከተብ ህፃናትን ከበሽታው እንዲታደጓቸው ጥሪ ቀርቧል።

    ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ

Viewing 2 posts - 1 through 2 (of 2 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.