Home › Forums › Semonegna Stories › የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ነው
Tagged: ምስራቅ አፍሪካ, ቲታንስ ዲ አፍሪቅ, የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር, የኤሌክትሮኒክ ግብይት, ጌታሁን መኩሪያ
- This topic has 3 replies, 2 voices, and was last updated 5 years, 10 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
December 23, 2018 at 1:47 pm #9053SemonegnaKeymaster
የሚገነባው የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል በኢትዮጵያ በቀዳሚነት በግል ዘርፉ የሚመራ ሆኖ መንግስት ክበባዊ ሁኔታን የማመቻቸት ሥራ ይሠራል። መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቦታ መረጣም ሆነ መሠረት ልማት በፍጥነት እንደሚያሟላም ተጠቁሟል።
አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ)– የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን መካከል ስምምነት ተደርጓል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን (Universal Postal Union) ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ቢሻር ሁሴን ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ሚኒስትሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት የቦታ አቅርቦትና መሠረተ ልማት የማሟላት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን ደግሞ ሥርዓቱን የመዘርጋት ኃላፊነቱን ወስዷል።
እንደ ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን ገለጻ፥ በአዲስ አበባ ይገነባል የተባለው ማዕከል በአፍሪካ ውስጥ ከሚገነቡ አራት ኢ-ኮሜርስ ማዕከላት አንዱ ሲሆን፥ ቀድሞ የምስራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ኬንያ ናይሮቢ ሊገነባ ታቅዶ የነበረው ነው። ወደ አገራችን የመጣበት ምክንያት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እያደገች መምጣቷ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያደርገው በረራ መበራከቱና የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዋንኞቹ ናቸው።
ተመሳሳይ ዜና፦ Chinese giant e-commerce Alibaba Group & its affiliate Ant Financial entering Ethiopian market
ማዕከሉ በኢትዮጵያ በቀዳሚነት በግል ዘርፉ የሚመራ ሆኖ መንግስት ክበባዊ ሁኔታን የማመቻቸት ሥራ ይሠራል። መንግስት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቦታ መረጣም ሆነ መሠረት ልማት በፍጥነት እንደሚያሟላም ጠቁመዋል።
የማዕከሉ መገንባት ከፍተኛ ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ አለው ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን፥ ለ100ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል። የአፍሪካ ምርቶች ለማንኛውም ሀገራት በቀላሉ እንዲታዩ በማድረግ ገበያውን በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር በኤሌክትሮኒክ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባና የገንዘብ ዝውውርን ለማቀላጠፍና የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ሚናውን ይወጣል። ዓለም በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሮኒክ ግብይት በጣም ርቆ መሄዱን ተከትሎ በአፍሪካ ደረጃ አስፍቶና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በዘርፉ ኢትዮጵያ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነች የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ዘመኑ የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ዓለም ነውና ከዓለም ጋር እኩል ለመጓዝ ማዕከሉን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። በዓለም ላይ እንደ አማዞን (Amazon)፣ አሊባባ ግሩፕ (Alibaba Group) እና የመሳሰሉ በኤሌክትሮኒክ ግብይት በዓመት እስከ አምስት ትሪሊን ዶላር እንደሚያንቀሳቅሱ ሁሉ በማዕከሉ አማካኝነት አገሪቱ ለማደግ የሚያስችላትን ተግባራት ሁሉ ትሠራለች ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
February 5, 2019 at 5:04 pm #9499AnonymousInactiveየኤሌክትሮኒክስ ግብይት በኢትዮጵያ ለመጀመር የአለም አቀፉ የፖስታ ድርጅት ቲክኒካል ኮሚቴ ጥናት ጀመረ፡፡
—–አፍሪካን በተለያዩ ቀጠናዎች ከፍሎ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ለመጀመር እየሰራ የሚገኘው ዓለማቀፍ የፖስታ ኅብረት (Universal Postal Union) አጥኚ ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ የላከው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው ስምምነት መሰረት ነው፡፡
ቡድኑ የኢትዮጵያ ዝግጁነት ከፖሊሲ፣ ከመሰረተ ልማትና ከኢ-ታክስ አኳያ፤ ኢትዮጵያ ስርዓቱን ለመዘርጋት ምን ማድረግ አለባት፣ ትግበራውን በምን መልኩ መከናወን ይኖርበታል የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ያጠናል፡፡
የግብይት ስርዓትን ለማዘመን፣ ገዢና ሻጭን በቀጥታ ለማገናኘት፣ ቀጠናዊ ትስስር ለመፍጠር፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ሃብት ለማሳደግ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰበው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት በኢትዮጵያ በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ እንደሚደረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ተናግረዋል፡፡
የአለም አቀፉ የፖስታል ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ማዕከሉን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት ማቀዱ ይታወሳል፡፡
በ2017 በአፍሪካ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ከ85 ቢሊየን እስከ 100 ቢሊየን ዶላር የገበያ ድርሻ ይይዛል ተብሎ ይገመታል፡፡
February 6, 2019 at 3:28 am #9523AnonymousInactiveኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ለመዘርጋት የጀመረችውን ስራ ዴንማርክ እንድታግዝ ጠየቀች፡፡
—–በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ካሪን ፖውልሰን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ጋር በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና በኤሌክትሮኖክስ ግብይት ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ዴንማርክ እንድታግዝና ቴክሎጂን በሚጠቀም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ዘረፍ እንድትሳተፍ ጠይቃዋል፡፡
1ቢሊየን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘውን ቡና እሴት ጨምሮ በኤሌክትሮኖክስ ግብይት ወደ ገበያ ማቅረብ ቢጀመር ገቢውን በ4 እና 5 እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን በኢትዮጵያ ለመጀመር የአለም አቀፉ ፖስታል ድርጅት ቴክኒካል ኮሚቴ ጥናት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
February 24, 2019 at 4:48 pm #9874AnonymousInactiveቡናን ከምርት እስከ ውጭ ገበያ ያለውን ሂደት በቴክኖሎጂ ለማገዝ ስምምነት ተፈረመ
—–‹‹ቲታንስ ዲ አፍሪቅ›› በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች በአፍሪካ ውስጥ የሚሰራ ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ቡናን ከምርት ጀምሮ እስከ ውጭ ገበያ ያለውን ሂደት በቴክኖሎጂ ለማገዝ ተስማምቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ‹‹ከቲታንስ ዲ አፍሪቅ›› ጋር ቴክኖሎጂን የሚጠቀም የግብርና ስራ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡
በዚህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ስራ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ እንደተያዘም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የቡና አምራች ሀገር ብትሆንም ዘርፉ በቴክኖሎጂ ባለመደገፉ እና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ባለመደረጉ ከዘርፉ የሚገባትን ያክል ተጠቃሚ አይደለችም፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ድርጅቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት የተስማማው፡፡
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው እና የቲታንስ ዲ አፍሪቅ ማኒጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ጊልበርት ሳጊያ ተፈራርመዋል፡፡
ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፍ የሚገባ በመሆኑ የትኛውንም ስራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተቋማዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
‹‹ቲታንስ ዲ አፍሪቅ›› አፍሪካ ውስጥ በቴክኖሎጂ የበለፀገ ማህበረሰብ ለመገንባት እየሰራ ያለ ድርጅት ነው፡፡
ምንጭ፡- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.