የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር አካዳሚ ግንባታ

Home Forums Semonegna Stories የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር አካዳሚ ግንባታ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • Author
    Posts
  • #7863
    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ኢ.ም.ባ.ኮ)– የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአፍሪካ (ኢ.ም.ባ.ኮ) ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የባቡር አካዳሚ በቢሾፍቱ ከተማ ለመገንባት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ባቡር አካዳሚ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብይ ጌታቸው ገለፁ።

    ለባቡር አካዳሚው ግንባታ የቻይና መንግስት ሳውዝዌስት ጂአኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ (Southwest Jiaotong University) ባካሄደው አማካሪ የአዋጭነት ጥናት መነሻነት የገንዘብ ድጋፍ የፈቀደ መሆኑን የገለፁት አቶ አብይ በተጠናው የአዋጭነት ጥናትና በኮርፖሬሽኑ ፍላጎት መሠረት የትግበራ ስምምነት (Implementation Agreement) እ.ኤ.አ ታህሳስ 19 ቀን 2017 ከቻይና ኤምባሲ የንግድና ኢኮኖሚክ ካውንስለር ቢሮ፤ እንዲሁም የግንባታ ዲዛይን መነሻ ሃሳብ (Scheme design) ጥር 6 ቀን 2018 እ.ኤ.አ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

    በግንባታው የዲዛይን መነሻ ሃሳብ መሰረትም የግንባታው የመጀመሪያ ዲዛይን (Preliminary Design) ተዘጋጅቶ በአሁኑ ወቅት በቻይና መንግስት በኩል ግንባታውን የሚያከናውን የኮንትራክተር መረጣ ሂደት ላይ መሆኑንና እስከ ቀጣይ ህዳር ወር ድረስ ኮንትራክተሩ ተለይቶ ግንባታው ከታህሳስ አጋማሽ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ሊጀመር እንደሚችልም አቶ ዓቢይ ገልፀዋል።

    ግንባታውን ተቆጣጥሮ በጥራት ከመረከብ በተጨማሪ ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ ማዘጋጀት ከኮርፖሬሽኑ ሃላፊነቶች አንዱ ሲሆን ለአካዳሚው ግንባታ ማስፋፊያውን ጨምሮ ከሚያስፈልገው 157.7 ሄክታር መሬት ውስጥ የ62 ሄክታር መሬት ከኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ እና ከከተማ መሬት ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ከክልሉ መንግስት ህጋዊ ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ዓቢይ የመሬት ፈቃዱ እንደተገኘ ዲዛይኑ ቀርቦ ግንባታው እንደሚጀመር፤ በተጨማሪም የግንባታ ግብዓቶችን ማምረቻ ሳይቶች ለኮንትራክተሩ ማቅረብ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን (ውሃ፣ መብራት…) ወደ ሳይቱ ማቅረብ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊነት መሆኑንና ይህን ተግባር የሚያከናውን ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን

    ከግንባታው ጋር ተያይዞ ከሥራ ቦታቸው ለሚፈናቀሉ የአካባቢው ማህበረሰበም በካሳ ክፍያ ብቻ የሚተው ሳይሆን በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን በማቅረብ፣ ቴክኒካል ድጋፍ በመስጠትና የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ፕሮፖዛል በማቅረብ ከክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ጋር በመሆን ህብረተሰቡን ያማከለ የተቀናጀ ልማት ፕሮፖዛል ቀርቧል ያሉት አቶ አቢይ የመሬት ፈቃዱ እንደተገኘ ወደ ሥራ እንገባለን ብለዋል።

    ኮርፖሬሽኑ በአካዳሚ ዘርፍ የባቡር አካዳሚ ከማስገንባት ባለፈም የባቡር ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማብቃት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለሙያዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሃገር ውስጥና በውጭ እያሰለጠ ይገኛል።

    በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ዙር ከ400 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በማስተርስ ፕሮግራም ያስተማረ ሲሆን የ1ኛ ዙር ተመራቂዎች ሁሉም በኮርፖሬሽኑ በስራ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አብይ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ዙር የተማሩት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ የሀገራዊ ሴክተሩን አቅም በመገንባት ለሚያከናውነው የራስ ኃይል ሥራዎች በመደራጀት ላይ በሚገኙ ቢዝነስ ዩኒቶች ስር ለስድስት ወር በሥራ ላይ ስልጠና በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    ምንጭ፦ ኢ.ም.ባ.ኮ

Viewing 1 post (of 1 total)
  • You must be logged in to reply to this topic.