Home › Forums › Semonegna Stories › የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም፣ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ እንዲደረጉ ወሰነ
Tagged: የሚኒስትሮች ምክር ቤት, የሰላም ሚኒስቴር, ፍጹም አረጋ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 6 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
October 12, 2018 at 4:48 am #8032SemonegnaKeymaster
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በተዘጋጀ ረቀቅ አዋጅ ላይ መክሮ እንዲጸድቅ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል።
በውይይቱ ላይ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ቀርቧል፦
- የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በቀሪው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አካክሶ ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጀት በማስፈለጉ፤
- አገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልና የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል አደረጃጀትን መከተል በማስፈለጉ፤
- የአስፈጻሚ አካላትን ቁጥር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ለማድረግ በማስፈለጉ፤
- ተደራራቢና ድግግሞሽ ሥልጣንና ተግባር የያዙ የመንግሥት ተቋማትን መቀነስ ወይም ለሥራቸው ቅርብ ከሆነ ሌላ የመንግሥት ተቋም ጋር እንዲዋሃዱ ማድረግ በማስፈለጉ፤
እንደሆነ በስብሰባው ላይ ተብራርቷል።
በምክር ቤቱም ውሳኔ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ተደርጓል፤ ዋና ዋናዎቹ ለውጦችም:-
- የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- በየሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው – የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ፤
- የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን
ወስኗል።
ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው ይገኛሉ።
ሌላው ቁልፍ ውሳኔ በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተወስኗል።
ከትምህርት ሚንስቴር ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመውሰድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር” ተብሎ እንዲደራጅ ተወስኗል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ሁለት ተቋማት ሆነው እንዲደራጁ ተወስኗል።
በአዲሱ አደረጃጀት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ቀርቶ በቀጣይነት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሠረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል። ይህም የመንግሥት ቁልፍ ሚና የሆነው ቁጥጥር (regulation) በልማት ድርጅቶች ላይ ካለው የባለቤትነት ሚና ተለይቶ እንዲታይ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
ረቂቅ አዋጁ ሌሎች መለስትኛ ለውጦችንም የያዘ ሲሆን፥ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.