Home › Forums › Semonegna Stories › የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ (ምርጫ ቦርድ)
Tagged: ሲዳማ, የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ, የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
- This topic has 1 reply, 2 voices, and was last updated 4 years, 5 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
November 23, 2019 at 4:10 pm #12761SemonegnaKeymaster
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም
ሀዋሳየደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕዝብ ውሳኔ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የሕዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈፀም ኃላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞን እና በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድልዎ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ አፈፃፀም መመሪያ በማጽደቅ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ወሳኔውን የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉ እና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስ ለሕዝብም ይፋ እንዲሆን ተደርጓል። ቦርዱ በሕዝብ ውሳኔው እቅድ አፈፃፀም ከክልሉና የዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይት እና ስምምነቶችን አድርጓል። በዚህም መሠረት ለሕዝብ ውሳኔ ማስፈፀሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግሥት እንዲፈቀድ ተደርጓል። ሕዝብ ውሳኔው በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈፀም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሠረት የሕዝቡ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚል ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃንና አዲስ በሚፈጠረው እና ነባሩ ክልል መሃከል የሚኖረውን የሃብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና በሕግ ማእቀፍ አውጥቶ አቅርቧል።
በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት በቦርዱ ባለሞያዎች የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል። በዚህም መሠረት ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የሕዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ ከዞኑ፣ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና አስተዳደር ተቋማት የሕዝበ ውሳኔው ፀጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል። የዕቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል ቆይቷል። ከቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ በዚህ ዕቅድ መሠረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።
ሕዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በሕግ መሠረት የሚያስፈፅሙ 6843 አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናውም ቀድመው የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ 20 አሰልጣኞች ለ5 ቀናት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ መመሪያ (manual) እንዲኖራቸው ተደርጓል።
የመራጮች ምዝገባ በዞኑ እና በሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛውም ሕጋዊ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 06 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበዋል።
የድምጽ ሰጪዎች ሕዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምጽ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልእክቶች ተላልፈዋል። በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብ እና የሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው የቦርዱ አመራር አባላት በሀዋሳ፣ በይርጋለም፣ በወንዶ ገነት፣ በበሌላ፣ በመዘዋወር የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶች እና የአሠራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እንዲሁም በድምጽ መስጠት ሂደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጓል። በደረሱት ጥቆማዎችም መሠረት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።
በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶች እና ቀደም ብሎ ከዞኑ እና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በሕዝበ ውሳኔው ሂደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ፦
- የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ጸጥታ አጠባበቅ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባ እና ድምጽ መስጠት ሂደት ሁለቱም አማራጮችን የሚወክሉ ወኪሎች አንዲገኙ ጥረት ተደርጓል፤
- የተጓደሉ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ ተደርጓል።
የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሠራሮች ትምህርት ለመውሰድ ለ128 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች እና 74 የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሂደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል እውቅና ተሰጥቷል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ተደርጓል። በኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካን መንግሥት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ሕዝበ ውሳኔን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል።
የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ ሲሆን በዚህም ሂደት 3000 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች እና 2.5 ሚሊዮን በላይ (መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኗል።
በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ጸጥታ እና ደኅንነት አስመልክቶ ቦርዱ ሂደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት አድርጓል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ እና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማኅበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል የጸጥታ አካላት፣ የፌደራል ፓሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተደርጓል።
ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል። በዕለቱ የቦርድ አመራር አባላት የመስክ ጉብኝቶችን ያካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቆጠራውም በዕለቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተለጥፏል። በዕለቱ ከመራጮች የሚመጡ ጥቆማዎችንም መሠረት በማድረግ የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ሲከናወኑ ውለዋል።
በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከተመዘገበው 2,280,147 መራጭ 2,277,063 ሰው ድምጹን ሰጥቷል። ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል። ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጠ ሰው ብዛት 33,463 ሲሆን የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጠ ሰው ብዛት 2,225,249 ነው። በውጤቱም ሻፌታ የመረጠው 98.51 % ሲሆን ጎጆን የመረጠው 1.48 % ነው። ። በሂደቱ የዋጋ አልባ ድምጽ ቁጥር 18,351(0.01%) ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱ ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሠረት፥ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል። የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሣኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል።
የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። ሕዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ ያምናል። በውጤቱ መሠረትም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና እምነት አለው።
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
የሕዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ በጎ ውጤት ሲሆን፥ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንጻር የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነው ብሎ ያምናል። የአፈፃፀም ሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ ለቀጣይ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤- የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፤ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት፤
- የሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሂደት የአንድን ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑ እና የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግሥት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ፤
- የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር፤
- በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማን የገጠር አካባቢ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅእኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት፤
- በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ፤
- በሕዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድር ተቋማት ኃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመት (projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ፤
- በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻ እና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅ እንደዋና ተግዳሮት የሚጠቀሱ ሲሆን (ማለትም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የደቡብ እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት) የሕዝበ ውሳኔ ቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የአካባቢ ጸጥታ እና ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ስምሪትን እንዲሁም ድምጽ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሰገን ድጋፍ ማድረጋቸው እና በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው።
ምስጋና
በሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ እስካሁን በአገራችን ከነበረው ልምድ የተለየ እና መጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም ችሏል። ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ቦርዱ ከተለያዩ አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ድጋፍ አግኝቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚከተሉት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናውን ያቀርባል።- በሕዝበ ውሳኔው በሰላማዊ እና ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ ለተሳተፉት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሙሉ፣
- ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ባልተሟላ አንዳንዴም በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔውን ላስፈጻሙ የሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች እና ሥራውን በማስተባበር ለደከሙ የቦርዱ ሠራተኞች፣
- ለሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች ምልመላ ድጋፍ ያደረጉልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ፣ ለአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስዳድር እና የርዕሰ መስተዳድሩ ሕህፈት ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን አስተዳደር፣
- ለሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣
- ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ እዝ፣
- ለፌደራል ፓሊስ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፓሊስ ኮሚሽን፣
- ለሲዳማ ዞን ፓሊስ፣
- ለሀዋሳ ከተማ ፓሊስ፣
- ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣
- ሕዝበ ውሳኔውን ለመታዘብ ለተሳተፉ ሲቪል ማኅበራት፣
- የተለያዩ እገዛዎችንን ላደረጉልን የአሜሪካን የልማት ድርጅት (USAID/IFES) እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP)፣
- ለአዲስ ፓርክ
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
June 18, 2020 at 11:03 pm #14857AnonymousInactiveየሲዳማ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ምላሽ ማግኘቱን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ተናግረዋል።
የሲዳማ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ምላሽ አግኝቷል
ሀዋሳ (ኢዜአ/ፋና) – የሲዳማ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት (ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መረጋገጥ) የሕገ-መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤት መሆኑን የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ገለፁ።
አፈ-ጉባኤው አቶ ለማ ገዙሜ ይህንን የገለፁት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የመጨረሻ ሕጋዊ ሂደት የሆነው የሥልጣን ርክክብን አስመልክቶ በሰጡት የእንኳን ደስ አላችሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ዓመታትን ያስቆጠረና መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል። በተለይ ከ2010 ዓ.ም. አጋማሽ የለውጥ ጉዞ በኋላ ቀደም ሲል በሕዝቡ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች እውቅና ተሰጥቷቸው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ በክልል የመደራጀት መብቱን በሕዝበ ውሳኔ ማረጋገጡን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የደቡብ ክልል ምክር ቤት የመጨረሻ ሕጋዊ ሂደት ሆነውን የሥልጣን ርክክብ ሥርዓት ማከናወኑን ያስረዱት አቶ ለማ ገዙሜ፥ ለመላው የሲዳማ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። የሕዝቡ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መረጋገጥ የሕገ-መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤት መሆኑንም ገልፀዋል።
“የሲዳማ ሕዝብ ለዘመናት ያቆየውን ከሌሎች ጋር ተዋዶ የመኖር እሴቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽኑ እምነት አለው” ብለዋል።
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም የተነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሕገ-መንግሥታዊ ሂደታቸውን ጠብቀው መልስ እንደሚያገኙ ጠቁመው በየአካባቢው ያሉ ሕዝቦች ጉዳዩን በትዕግስት መከታተል እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ለመላው የሲዳማ ሕዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ፋና) ዘግቧል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው እንደገለጹት፥ የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር የረጅም ዘመናት ጥያቄ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ምላሽ አግኝቷል።
የሲዳማ ሕዝብ ከሌሎች የክልሉ ሕዝቦች ጋር በጋራ ተቻችሎና ተግባብቶ የኖረ ደማቅ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ቀደም ሲል የነበረው አንድነት መተሳሰብና አብሮነት የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ክልል ለአስተዳደራዊ ሥራ የሚያገለግል እንጂ በሕዝቦች መካከል ድንበር ማኖር እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ርስቱ፥ የሕዝቡ የቆየ መቻቻል እና እርስ በርስ መደጋገፍ ከምን ጊዜውም በላይ ልቆ እንዲጠነክር ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከአዲሱ የሲዳማ ክልል ጋር በመቀናጀት ለጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ጠንክሮ በመሥራት የሀገራችንን እድገት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንተጋለን ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የሲዳማ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ምንጮች፦ ኢዜአ/ፋና
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.