Home › Forums › Semonegna Stories › የሳይንስ ሳምንት በኢትዮጵያ፡ ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 2 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 5, 2019 at 11:52 pm #12517SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሳይንስ ሳምንትን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ህዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት ያከብራል።
የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ዓላማዎችና መሪቃል ይከበራል። የኢትዮጵያው የሳይንስ ሳምንት ሲከበር የተባበሩት መግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) በየዓመቱ ኖቬምበር 10 ቀን የሚያከብረውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ባማከለ ሁኔታ ይፈፀማል።
ይህ ሀገራዊ የሳይንስ ሳምንት ሲከበር ዋና ዓላማው ሳይንሳዊ አስተሳሰብንና አሠራርን፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ ሥራዎቻችንን ለማሳወቅና እንዲሁም በተለያዩ ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በቀጣይም የወጣቱን ትውልድ የሳይንስ ፍላጎት ለማሳደግ እንዲያግዝ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሳይንስን፣ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን እና የሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ያለመ ነው።
በሳይንስ ሳምንት ከሚከናወኑ ዝግጅቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- ከጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል በSTEM (Science, Technology, Engineering, and Mathematics) ዘርፎች ውድድር ይካሄዳል። ተማሪዎቹ በአራቱ የትምህርት ዘርፎች ለውድድር በሚያቀርቡት ፈጠራ ላይ ተመሥርቶ በሚሰጠው ዳኝነት አሸናፊዎች እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ተሸላሚ ይሆናሉ።
- ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶችና ሙያ ማኅበራት ጋር በሒልተን ሆቴል ምክክር ያደርጋል:: በምክክር መድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሳይንስ ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫ፣ የሙያ ማኅበራት ሚና ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና፤ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕይታ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አደረጃጀቶች የሳይንስ ሥራዎች ትኩረትና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “ለኢትዮጵያ ግብርና አገር በቀል እይታ” በሚል የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ ይካሄዳል።
- አርብ ጥቅምት 28 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር ወርክሾፕ ይካሄዳል።
- እሁድ ጥቅምት 30 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀን (Green Day) ይከበራል። በዕለቱ ባለፈው ክረምት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተተከሉ ችግኞችን ቦታቸው ድረስ በመገኘት የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉ። እፅዋቱ ባሉበት ደረጃ በሚሠሩ የእንክብካቤ ሥራዎች ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ሳይንሳዊ ገለፃ ይቀርባል።
- ሰኞ ሕዳር 01 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biodiversity Institute) ጋር በመተባበር “ሰውና ሥነ ምህዳር (Man and Biosphere)” በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል። በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጥሮ ሳይንስና ግብርና ኮሌጆች በርዕሱ ላይ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል።
- ማክሰኞ ሕዳር 02 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (Ethiopian Biotechnology Institute) ጋር በመተበባር “ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ ገለፃ ይቀርባል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር “ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል ርዕስ ሳይንሳዊ ገለፃዎችና ውይይቶች ይካሄዳሉ።
ስለሆነም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት 25 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በሚጀምረው የሳይንስ ሳምንትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውት ለህብረተሰቡ የሚመጥኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን የሚፈጥሩ ሥራዎችን በመሥራት የሳይንስ ሳምንት አከባበር አካል እንዲሆኑ እንጋብዛለን።
በተጨማሪም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና (Science for Ethiopia’s Development and Prosperity)” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የሳይንስ ሳምንት፣ በየዘርፋቸው ሳይንስ ለአገር ልማትና ብልፅግና ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በበዓሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.