አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።
አዳማ (የትምህርት ሚኒስቴር) – በአገሪቱ እስከ ታኛናው መዋቅር ያሉ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሚያስችል አገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ተመሠረተ።
ክቡር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ መሀመድ አህመዲን በአገር አቀፍ የተማሪ ወላጆች ህብረት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት የህብረቱን ዓላማ በየደረጃው ባለው መዋቅር የትምህርት ተቋማትና የተማሪ ወላጆችን በማስተሳሰር በሁለንተናዊ ብቃት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት ረገድ የወላጆችን ሚና ለማሳደግ ነው።
በትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ተግባር የወላጆች ሚና ማሳደግ፣ በወላጆች፣ በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለውን ግንኙት ውጤታማ ማድረግ፣ ጤናማ የመማር-ማስተማር ሂደት በላቀ ደረጃ እንዲረጋገጥ የወላጆችን ተሳትፎ ማሳደግና ለትምህርት ሥራ ማጎልበት የሚያስችል አደረጃጀትና ትስስር መፍጠር የህብረቱ ቀሪ ዓላማዎች መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል።
በህብረቱ ምሥረታ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ547 የሚበልጡ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት ሲሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት በጸሀፊነት የሚያገለግሎ ወላጆችን ምርጫ ተካሂዷል።
በዚህም መሠረት ኢንጅነር ጌታቸው ሠጠኝ ከአዲስ አበባ የህብረቱ ሊቀመንበር ፣ወይዘሮ መሠረት ተክሌ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የህብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ፣ አቶ ሀሰን በዳሶ ከኦሮሚያ የህብረቱ ጸሀፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ህብረቱ በተጨማሪ 11 አባላት ያሉበትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን በዚህም መሠረት ከትግራይ አቶ ጸጋዬ አለማየሁ፣ ከአፋር አቶ አሊ የጦ፣ ከአማራ አቶ አዱኛ እሸቴ፣ ከሱማሌ አቶ ኻሊድ አብዱልቃድር፣ ከደቡብ አቶ ተሻለ አየለ፣ ከጋምቤላ አቶ አእምሮ ደርበው፣ ከሐረሪ ወ/ሮ ፋጡማ አብዱ በህብረቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተመርጠዋል።
የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጆች ህብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር ጌታቸው ሰጠኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህብረቱ ለትምህርቱ ሥራ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ህብረቱ ለፍኖተ-ካርታው መተግበር ጠቃሚ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው ህብረቱ ለሚያከናውነው ተግባር ውጤታማነት የትምህርት ሚኒስቴር እገዛ እንደማይለየው አስታውቀዋል።
ህብረቱ በቀጣይ በሰላምና ደህንነት፣ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ተቋማት ፋይናንስ አስተዳደር ጉዳዮች የሚያተኩሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች በቀጣይ ተቋቁመው ወደሥራ እንደሚያስገባም በዚሁ ጊዜ መገለጹን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል።
ምንጭ፦ የትምህርት ሚኒስቴር