በጥቅምት ወር ሁለተኛ ሳምንት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች 78 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ግጭት በመቀሰቀስ የተጠረጠሩ 409 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ (ፋና) – ከጥቅምት 11 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. ክስተት ጋር ተያይዞ ግጭት በመቀስቀስ የተጠረጠሩ 409 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ላይ በወቅቱ በነበረው ግጭት የ78 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አንስተዋል።
በወቅቱ በግጭቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የፀጥታ መዋቅሩ በሙሉ አቅሙ መሥራቱንም ነው የገለፁት። የጸጥታ አካላት ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለማረጋጋት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ችግሩን ለማርገብ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት አስተዋፀኦ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል።
በሀገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ተመሳሳይ ግጭቶች ከተጠረጠሩ 3 ሺህ 221 ግለሰቦች መካከል ከ2 ሺህ በላዩ ለሕግ መቅረባቸውን አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግርዋል።
የህብረተሰቡን ደኅንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ክስተቶች እየሰፉ በመምጣታቸው ሰላምን የማስከበር ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጠው መንግሥት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አንስተዋል፡፡ ማንም ከሕግ በላይ ስላልሆነ በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ አካል ላይ ተጠያቂነት እንደሚረጋገጥም አስታውቀዋል።
አቶ ንጉሱ ጥላሁን በመግለጫቸው፥ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ከለውጡ ትሩፋቶች መካከል አንደኛው የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት መሆኑን አንስተዋል። ሆኖም አንዳንድ መገናኛ ብዙኃንና የማህበረሰብ አንቂዎችን ነጻነት ሽፋን በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ መረጃዎችን እያሰራጩ በመሆኑ የመቆጣጠር ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ከኢህአዴግ ውህደት ጋር በተያያዘም አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው በሀገሪቱ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት ታስቦ የመጡ ሃሳቦች ሆን ተብሎ ባልተገባ መንገድ እየተተረጎሙ ለሕዝብ ማደናገሪያነት እየዋሉ ነው ብለዋል – አቶ ንጉሱ ጥላሁን። ሃሳቡ ፓርቲው ለበርካታ ዓመታት ሲመክርበት የቆየ፣ በጥናት የተደገፈና የበርካታ የሰለጠኑ ሀገራት የተቀመረበት አሁን ለደረስንበት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የሚመጥን ሃሳብ ነው ብለዋል። ከዚያም ባለፈ የአገሪቱን ህዝቦች ከባለቤትነትና ደጋፊነት ወደ እኩልነትና በአንድ ድምጽ ወደ መወሰን የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ