አሁን የተወሰደውን እርምጃ በማፋጠን ጣቢያውን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የመለዋወጫ አቅርቦት ስምምነትም ጣቢያውን ከገነባው ኩባንያ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከነበሩት አራት ተርባይኖች ሦስቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ አስታወቁ።
በተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ዶ/ር አብርሃም፥ ለጣቢያው በተሰጠው ትኩረትና በተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ቀደም ሲል በአንድ ተርባይን ብቻ ኃይል ያመነጭ የነበረው ጣቢያው በአሁኑ ሰዓት ሦስት ተርባይኖቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።
አሁን የተወሰደውን እርምጃ በማፋጠን ጣቢያውን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የመለዋወጫ አቅርቦት ስምምነትም ጣቢያውን ከገነባው ኩባንያ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር አብርሃም በላይ ገለፃ፥ በኃይል ማመንጫው የተከሰቱ ችግሮች በወቅቱ ተለይተው መፍትሄ እንዲያገኙ ባለመደረጉ ተቋሙ ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ተገዷል። በመሆኑም ተመሳሳይ ችግር በሌሎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንዳያጋጥም ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባም አንስተዋል።
ዶ/ር አብርሃም ከጣቢያው ሠራተኞች ጋር የተወያዩ ሲሆን በተቋሙ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቋሙ የተሻለ አቅም እንዲኖረው እና በአገልግሎት ጥራቱ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ የሰው ሃብት ልማት ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ተቋሙ ዋናው የኦፕሬሽን ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችሉ የተልእኮ ግልፅነት የመፍጠር፣ የኮርፖሬት ቢዝነስ አስተሳሰብ የመገንባት፣ አገልግሎት የሚሰጡ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ የማስገባት፣ የግሪድ ሞደርናይዜሽን፣ የሀብት አስተዳደርና የፋይናንስ ስርዓቱን የማዘመን የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም በውይይቱ ተብራርቷል።
በ2002 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተከዜ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የደጋን ቅርፅ ያለው ሲሆን በግንባታው ዘርፍ በአፍሪካ ጉልህ የኢንጂነሪንግና ዲዛይን ፋይዳ ካላቸው አስር የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ውስጥ አንዱ ያደርገዋል።
185 ሜትር ከፍታና 710 ሜትር ርዝመት ያለው የተከዜ ግድብ 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን በዓመት በአማካይ 1431 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ያመነጫል።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦