የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ያዘጋጁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ መውጣቷም ተገልጿል።
ደብረ ብርሃን (ሰሞነኛ)– በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማኅበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የቱሪዝም ሳምንት ጥር 24/2011 ዓ/ም የቁንጅና ውድድር በማካሄድ ተጠናቀቀ።
በውድድሩም ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ያብፀጋ አይነኩሉ ከሁለተኛ ዓመት የሎጅስቲክና ሰፕላይ ቼን ማኔጅመንት (Logistics and Supply Chain Management) ትምህርት ክፍል ተመርጣለች። በሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ኤልሳቤጥ ደስታ የ3ኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ (Biotechnology) እና በሦስተኛነት ደረጃ ተማሪ ትንሳኤ ፀጋዬ አንደኛ ዓመት የሳይኮሎጂ (Psychology) ትምህርት ክፍል እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
◌ VIDEO: The Yellow Movement AAU: Speaking up for women and girls – empowering women (Ethiopia)
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶ/ር ጌትነት አሸናፊ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከሳምንት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርስቲው ግቢና ውጪ ያለውን አካባቢ በማጽዳት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራት በማከናወን የቆዩ መሆናቸውን በመግለፅ ላደረጉት በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
የቱሪዝም ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ኪዳኔ እንደገለፁት የዘንድሮው ውድድር ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፥ በባለፈው ዓመት የተመረጠችው ወ/ሪት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፋ 3ኛ ደረጃ በመውጣቷ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘች መሆኗን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ለጓሳ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ መታሰቢያነት ‹‹ቱሪዝም ለአካባቢ እንክብካቤና ለማህበረሰብ አቅም መጎልበት›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የቱሪዝም ሳምንት 8 /ስምንት/ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈው የቁንጅና ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የወጡትን አሸናፊዎችን በመምረጥና እውቅና በመስጠት በዓሉ ተጠናቋል።
ምንጭ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦