የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሰጠው መግለጫ፥ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት አሁን የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሂደት በተገቢው ጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባው ነው በማለት አስታውቋል።
ሰብዓዊ ጥሰትና ሙስና በፈጸሙ ሰዎች ላይ በመንግስት ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የህግ ልዕልና ሳይሸራረፍ ከተጽዕኖ በጸዳ መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት መግለጫው አመልክቷል።
የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።
በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሙስና ችግርና ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ውስጥ እጃቸው ያለ አመራሮችና ተቋማት ስለመኖራቸው ቀደም ሲል በተካሔዱ የኢህአዴግ መድረኮች ውይይት መደረጉንም አመልክቷል።
ችግሩ በእኩል እንዲስተናገድ ከማድረግ ባለፈ እርቅና ይቅር ባይነትን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሂደት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሷል።
“የህግ የበላይነትም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚጠይቅ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ያምናል” ብሏል መግለጫው።
የትግራይ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የከፈለው መስዋዕትነት የዜጎች እኩልነትና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንጂ በማንም አካል እንዲጣስ እንዳልሆነ መግለጫው አመልክቷል።
ባለፉት ዓመታት ይታዩ የነበሩት የፍትህና የዲሞክራሲ መጓደሎች እንዲስተካከሉ ሕዝቡ በጽናት እየታገለ መምጣቱንም መግለጫው አስታውሶ በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል።
ከሰብአዊ መብት አያያዝና ከሙስና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እየታየ ላለው ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እጃቸው ያለበት አመራሮችና ተቋማት መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ሰሞነኛ ኢትዮጵያ |