Home › Forums › Semonegna Stories › ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
Tagged: አብን, የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 12 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
January 27, 2020 at 1:31 am #13441SemonegnaKeymaster
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት ጥር 16 እና 17 ቀናት 2012 ዓ.ም. 5ኛ መደበኛ ጉባዔውን በማካሄድ የንቅናቄያችንን አጠቃላይ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ፣ የምርጫ ዝግጅት፣ የታሠሩ የአብን አመራሮችና አባለትን፣ የታገቱ አማራ ተማሪዎችን እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔ እና አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቋል።
በአገራችን ኢትዮጵያ አማራ-ጠል የተሳሳተ ትርክት በፈርጣጭ ብሔርተኞች መቀንቀን ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያሳለፈ ቢሆንም፥ ለሦስት አስርት ዓመታት መዋቅርና ሕግ ሆኖ አማራን እንደ ሕዝብ ለመጨቆን ሥራ ላይ ውሏል። የአማራ ሕዝብ የተገንጣይ ብሔርተኞች የተሳሳተ ትርክት እንዲቆም ብሎም ኢትዮጵያዊያን በሰላምና በአንድነት ተከባብረው እንዲኖሩ ሲታገል ቆይቶ በ2010 ዓ.ም. ለውጥ እንዲመጣ ቢያድርግም ለውጡን እንመራለን እና እናሻግራለን የሚሉት “ተረኛ ነን” ባዮች የቆየውን ትርክት ለማስቀጠል በሚያደርጉት ልፊያ ሕዝባችን በተደጋጋሚ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።
የአማራ ሕዝብ በሰላምና በመተሳሰብ እሴቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ተዋዶና ተከባብሮ የኖረ ወደፊትም የሚኖር ሕዝብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ሀቅ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያዊያንን የቆየ እሴት የማይወክሉ ብሎም እንቆምለታለን ብለው የሚምሉለትን ሕዝብ ዓላማና ፍላጎት የማያውቁ ተገንጣይ የፖለቲካ ቡድኖች በሚያቀነቅኑት የአማራ-ጠል ትርክትና እንቅስቃሴ የተነሳ የአማራ ሕዝብ ለከፍተኛ ጭቆና ተዳርጎ ቆይቷል። የአማራ ሕዝብ ትግል የኅልውናና ፀረ-ጭቆና መሆኑ የታወቀ ሲሆን፥ ባለፉት ዓመታትም ጭቆናን ሲታገል የነበረው አንደኛው ጨቋኝ በሌላኛው ጨቋኝ እንዲቀየር አልነበረም፤ አይደለምም። ሆኖም ግን “የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት መንሳት” የሚለው ትህነጋዊ ትርክት በተረኛ መንግሥት ነን ባይ ቡድኖችና ተቀፅላዎች በመተካቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት በ5ኛ መደበኛ ጉባዔው በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔና አቅጣጫ አስቀምጧል።
የታገቱ አማራ ተማሪዎችን በተመለከተ፡-
በደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ አማራ ተማሪዎች ታግተው ከጠፉ ሁለት ወራት አልፈውታል። ይህ የአሸባሪነት ተግባር በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠውና የታገቱ ልጆች እንዲለቀቁ አብን መጠየቁ ይታወሳል። የአማራ ሕዝብ እና ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይህን ነውረኛ የአሸባሪነት ተግባር አውግዞ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በትዕግስት ሲጠይቅ ቆይቷል። የአብን ብሔራዊ ምክር ቤት በዚህ የአሸባሪነት ተግባር የታገቱ አማራ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ አሸባሪዎችም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እያሳሰበ፤ ለታገቱ አማራ ተማሪዎች ድምፅ ለማሰማት በተለያዩ ከተሞች በአማራ ወጣቶች የተጠራውን ሰልፍ አብን የሚደግፍ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሰላማዊ ሰልፉም ከየትኛውም ጥቃትና ጥፋት ነፃ በሆነ መንገድ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ የማድረግ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እናሳስባለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ “ክልል” መንግሥትና ማዕከላዊ መንግሥቱ ላሳዩት የበዛ ቸልተኝነት ተጠያቂነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጊቱን ላልተገባ የፖለቲካ ቁማር ከማዋል ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በጥብቅ እናሳስባለን። መላው የአማራ ሕዝብ ቀጣይ በልጆቹ ዙሪያ መንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ እየተከታተለ ለቀጣይ ትግሎችም ራሱን እንዲያዘጋጅ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
የፖለቲካና የኅሊና እስረኛ የሆኑ የአብን አመራርና አባላትን በተመለከተ፡-
የአማራ “ክልል” ከፍተኛ አመራሮች እና የፌዴራል የጦር መኮንኖች ግድያ ተከትሎ “የክልሉ”ም ሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከመሆኑም በላይ ካላንዳች የፖለቲካ ትርፍ ስሌት ኃቁን በወቅቱ ለሕዝብ ማቅረብ ሲገባቸው፤ በሕዝብ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ በደል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ይባስ ብሎ ንጹሃን የንቅናቄያችን አመራሮችና አባሎቻችንን በታሪክ አጋጣሚ መንግሥት የመሆን ዕድል የገጠመው ቡድን ለአማራ ሕዝብ ካለው የተሳሳተ የጥላቻ አመለካከት በመነሳት በግፍ አግቷቸው እንደሚገኝ ይታወቃል። ገዢው መንግሥት የንቅናቄያችንን አመራሮችና አባላት በቂ ባልሆነ ማስረጃ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ አቆይቷቸዋል።
የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ብሎም የአገርን ኅልውና ግምት ውስጥ በማስገባት ያለአግባብ የታሰሩ የአብን አመራሮችና አባላት በውይይት እንዲፈቱ ከ7 ወራት በላይ ኃላፊነት በተሞላበት እጅግ ከፍተኛ ትዕግስት የጠየቅን ከመሆኑም በላይ ጓዶቻችን ያልተገባ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ። ይህንንም አስመልክቶ ንቅናቄያችን ለሕዝብና ለመንግሥት በተከታታይ ያሳወቀ ቢሆንም ከመንግሥት በኩል ፍትህ በመነፈጉ ምክንያት ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ቀጣይ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን ለመጠቀም ተገደናል። ስለሆነም መንግሥት ያለአግባብ በአፈሳ የፈፀመውን እስር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ክሳቸው ተቋርጦ በአንድ ወር ውስጥ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እያሳሰብን፤ በተቀመጠው ጊዜ የማይፈቱ ከሆነ በየደረጃው ያሉ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ሕዝባችንን በማስተባበር እንደሚከተለው በተገለጸው የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ሁሉንም የሰላማዊ ትግል አማራጮች እንተገብራለን።
-
- የካቲት 22/2012 ዓ.ም፡- በተመረጡ የአገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፤
- የካቲት 26 እና 27/2012 ዓ.ም፡- አድማ ይደረጋል፤
- ከመጋቢት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ አመራሮቻችን እና አባሎቻችን እስከሚፈቱ ድረስ ለተከታታይ ቀናት ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲካሄድ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ የወሰነ ሲሆን ለዚህም ከወዲሁ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ስለተፈናቀሉ ተማሪዎች፡-
መንግሥት አገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በሰላም ትምህርታቸውን መከታተል ካለመቻላቸውም በላይ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና የሞት አደጋ ገጥሟቸዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የዩኒቨርሰቲ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ይህ በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸም በደል አማራ ላይ የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር ሲደረግ የኖረው መንግሥታዊ ጭቆና መገለጫ መሆኑን አብን ይገነዘባል። ስለዚህ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተማሪዎቹ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትን መንገድ በአስቸኳይ እንዲያመቻች አብን ያሳስባል።
አገራዊ ምርጫን በተመለከተ፡-
ንቅናቄያችን ያዘጋጀው የምርጫ ማኒፌስቶ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ምክር ቤቱም ተጨማሪ ጉዳዮች ተካተውበትና በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግበት እንዲሁም ንቅናቄያችን በቅርቡ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲፀድቅ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በመጨረሻም በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያለ መላው የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ቡድን የሚፈጸምን ኢ-ሰብአዊና የአሸባሪነት ተግባር ተባብሮ እንዲያወግዝ ብሎም ለፍትኅ፣ እኩልነትና ነጻነት እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋጋጥ እንዲታገል ንቅናቄያችን ጥሪውን ያስተላልፋል።
አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!
የአማራ ብሔራዊ ነቅናቄ (አብን) ብሔራዊ ምክር ቤት፤
ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
-
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.