Home › Forums › Semonegna Stories › የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር የ2012 ዓ.ም. መማር ማስተማርና የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አደረገ
Tagged: ብርሃኑ ነጋ, አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ, ጣሰው ወልደሃና, ፋሲል ንጉሴ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 4 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
September 11, 2019 at 5:39 pm #11933SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር የ 2012 ዓ.ም. መማር ማስተማርና የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አደረገ። ዶ/ር ፋሲል ንጉሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ከ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች በ4 ዓመት ቆይታ ጊዜአቸው ተማሪዎቹን መሠረታዊ ዕውቀት ሊያስጨብጧቸው የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች እንደሚሰጡና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የዝግጅት ምዕራፍ እንደተወጠነ ገልጸዋል።
“ለሰላም መደፍረስ መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን እየለየን ከሚመለከታቸው ጋር በማቀናጀት መፍትሔ እንዲያገኙ እንጥራለን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱ መስመሩን ጠብቆ እንዲሄድ የቁጥጥር ሥርዓቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ ብሔርን፣ ሀይማኖትንና ፖለቲካን መሠረት ያላደረጉ የዶርም ድልድሎችን እናደርጋለን” በማለት ዶ/ር ፋሲል በ 2012 ዓ.ም. ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የምንከተላቸው አቅጣጫዎች በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለጻ (presentation) ላይ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናም የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን የጠቆሙትን ሲያጠናክሩ “ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በብሔር እየተደራጁ የሚመጡ ማናቸውም ዓይነት የተማሪዎች አደረጃጀት፣ የተማሪዎች ክበባት… ወዘተ አናስተናግድም” በማለት አሳስበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተፈጥረው በነበሩ ብሔር-ተኮር የተማሪዎች ግጭትን አስመልክተው ዶ/ር ፋሲል የሚከተለውን ብለዋል፥ “ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲያችን ውስጥ በብሔርና በሃይማኖት መሰባሰብ፣ መከፋፈል፣ መጣላት፣ መደባደብ የንብረት የአካልና የሕይወት መጥፋት ጉዳት የማድረስ እኩይ ተግባራት እንዳይኖሩ ተቋማችን ጠንክሮ ይሠራል” በማለት አስረድተዋል።
በዋነኝነት ለ 2012 ዓ.ም. አዲስ ገቢና ነባር የቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ተማሪዎች የሚደረግላቸውን የአቀባበልና የመተዋወቂያ ገለጻ (orientation) አሰጣጥን አስመልክተው ፕሮፌሰር ጣሰው ሲያብራሩ፥ “ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ መዋል የሚጀምር በተማሪዎች፣ በወላጆቻቸውና በዩኒቨርሲቲያችን መካከል የሚፈረም ውል ይኖረናል፤ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲያችን እንደገቡ በቅድመ ምረቃ ትምህርት አስተባባሪዎች እና ነባርና ልምድ ባላቸው መምህራን ስለ ዩኒቨርሲቲያችን አጠቃላይ መረጃ ይሰጣቸዋል፤ የመጀመሪያ ዓመት ለሆኑት ተማሪዎች ስለሚወስዷቸው የትምህርት ዓይነቶችና ፋይዳቸው፣ ስለተማሪዎች ሥነ-ምግባር መመሪያና ስለተቋማችን ሥነ-ሥርዓት፣ ሕግና ዲሲፕሊን ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲያገኙ ይደረጋል” በሚል ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የምጣኔ ሃብት መምህርና በአሁን ጊዜ የተቋሙ የቦርድ አባል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተቋሙ በሚሻሻልበት ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ሲሰጡ ተቋሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማዘመንና ከሌሎች ታዋቂና ስመ-ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እንዲመደብ ለማስቻል የመምህራን፣ የአስተዳደር፣ የማህበረሰቡና የመንግሥት ርብርብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደሃገር እንድንቀጥል ባሉት ገለጻቸው ሲናገሩ፥ “የሃገሪቱ የትምህርት አወቃቀር የሚሻሻልበትን አቅጣጫ እንቀይስ፤ ፈጣሪና አምራች ዜጋ እንድናገኝ ተማሪዎቻችንን በጥልቀት የሚያስቡና የሚያስተውሉ እናድርጋቸው፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ጠቃሚ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበትና ልቆ የተገኘው ሃሳብ ተደማጭነትን አግኝቶ የሚተገበርበት ቁልፍ ቦታ እናድርገው” በሚል ገለጻቸውን ሰጥተዋል።
ምንጭ፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.