Home › Forums › Semonegna Stories › “መንግስት ዜግነታችንን የካደ ግፍ ፈጽሞብናል” ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ውስጥ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች
Tagged: ለገዳዲ, ለገጣፎ, ሰመጉ, የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 11 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 28, 2019 at 2:28 am #9959SemonegnaKeymaster
ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ መኖሪያ ቤታቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ጠይቋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ለገጣፎ ከተማ፣ የዜጐች መኖሪያ ቤት መፍረሱ በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው የተባበሩት መንግስታት (ተመድ)፥ ጉዳዩን በትኩረት እንደሚመረምር አስታውቋል። በተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ ቤት ምጣኔ ኃላፊዋ ለይላኒ ፋራህ (Ms. Leilani Farha) እንደገለፁት፥ በለገጣፎ 12ሺህ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቤት አልባ አድርጐ፣ ለእንግልት ይዳርጋል፤ ይህም ግልጽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል።
ስለ ቤቶቹ መፍረስ መረጃው ለተቋማቸው መድረሱን ያረጋገጡት ለይላኒ ፈራህ፥ በቀጣይ ጉዳዩ በልዩ መርማሪዎች ተመርምሮ፣ በዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወገኖች እንዲጋለጡ ይደረጋል ብለዋል። የዜጐችን መኖሪያ ቤት በዚህ መልኩ ማፍረስ በተባበሩት መንግስታት፣ ሀገራት ቃል ኪዳን የገቡለትን የማንኛውም ዜጋ፣ መጠለያ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት በእጅጉ የሚፃረር ነው ብለዋል – ኃላፊዋ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በለገጣፎ ዜጐች መጠለያ አልባ መደረጋቸውን በጽኑ አውግዞ፥ ቤት ለፈረሰባቸው ወገኖች፣ የፌደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና ተመጣጣኝ ካሣ በአስቸኳይ እንዲያቀርብ እንዲሁም እየተካሄደ ያለው የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስና ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው።
ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም!!
በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በ01 እና 02 ቀበሌዎች፣ ጭላሎ፣ ወበሪ፣ ለገዳዲ ቄራ፣ ገዋሳ፣ እና በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን “ህገወጥ ግንባታዎች ናቸው፤ ለአረንጓዴ ልማት ይፈለጋሉ” በማለት ከየካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በኃይል በማፍረስ ላይ ይገኛል። የከተማዋ ከንቲባ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁትም በቀጣይም ከ12 ሺህ በላይ ቤቶችን እንደሚያፈርሱም አረጋግጠዋል። ሰመጉ ስለጉዳዩ የከተማዋን ከንቲባ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ሰመጉ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ዜጐች እንዳስረዱት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግስት ላይ እምነታቸውን ጥለው በተለያየ ወቅት በገዙት ቦታ ላይ የገነቡትን መኖሪያ ቤቶች በመገንባት እና አካባቢ በማልማት ከተማዋን ለእድገት አብቅተዋታል። በእነዚሁ ዓመታት ውስጥም የአካባቢው የመንግስት ኃላፊዎች እያወቁት የመብራት እና ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፣ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን፤ በተለያዩ አስተዳደራዊና የልማት እንቅስቃሴ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የከተማዋ አስተዳደር ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር ከነዋሪዎች ጋር በቂ ምክክር ሳያደርግ እና ሊመጣ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይኖረው ቤቶችን በማፍረስ ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል። በዚህም የዜጐችን ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ የመኖርን መብት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ምግብ የማግኘት መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መብቶች ተጥሰዋል።
የከተማው አስተዳደር የወሰደውን የኃይል እርምጃ ይበልጥ አስከፊ እና አጠያያቂ የሚያደርገው ከመኖሪያቸው በ7 ቀናት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በኃይል እንዲፈናቀሉ ለተደረጉ ዜጐች ምንም ዓይነት አማራጭ የመኖሪያ ስፍራም ሆነ ጊዜያዊ የመጠለያ ስፍራ ያልተዘጋጀላቸውና ሰብዓዊ እርዳታም ያልተደረገላቸው መሆኑ ነው።
የፌዴራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዜጐች ላይ እየተፈፀመ ያለውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፤ እየተካሄደ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስና ዜጐችን ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ መኖሪያቸው ለፈረሱባቸው ዜጐች ተገቢዉን ድጋፍ እና ተመጣጣኝ ካሳ በአስቸኳይ እንዲያደርጉና በሠላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስጠብቁላቸው ሰመጉ ይጠይቃል።
ምንጮች፦ አዲስ አድማ ጋዜጣ፣ ሰመጉ፣ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.