Home › Forums › Semonegna Stories › የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ የሆነውን የዲጂታል ማዕከል ከፈተ
Tagged: ባጫ ጊና, የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 11 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
January 26, 2020 at 1:10 am #13428AnonymousInactive
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በሀገራችን ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የክፍያ ሥርዓቶችን በማስተዋወቅ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የዲጂታል ማዕከል ከፈተ።
ይህ የዲጂታል ማዕከል በቀን ከ300 ሺ ሰው በላይ በሚንቀሳቀስበትና ከፍተኛ የደንበኞች ፍሰት ባለበት መገናኛ አካባቢ፣ የባንኩ ህዳሴ ህንፃ ላይ ነው የተከፈተው።
በዲጂታል ማዕከሉ መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና እንዳሉት፥ ማዕከሉ ከሃያ በላይ የገንዘብ መክፈያና መቀበያ ማሽን በአንድ ቦታ በማስቀመጥ ደንበኞች በቀላሉ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገራችንን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ፋና ወጊ መሆኑን ገልፀው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ከ16 ዓመታት በፊት የኤቲኤም ማሽንን (ATM) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀውና አገልግሎት ላይ ያዋለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑም አቶ ባጫ አስታውሰዋል።
በዲጂታል ማዕከል ውስጥ ከተቀመጡ በርካታ ኤቲኤሞች መካከል ሁለቱ ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግ እንዲችሉ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልፀው፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ገንዘብ ገቢና ወጪ የሚያደርጉ ከ100 በላይ ተጨማሪ ኤቲኤሞችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚቀመጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጣቸው የባንክ አገልግሎቶች ጥራታቸውን ጠብቀውና የደንበኞችን ፍላጎት አሟልተው እንዲሰጡ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ። ይህ የተገለጸው ባንኩ የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በዝርዝር ገምግሞ በቅርንጫፎች እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ነው።
አቶ ባጫ ጊና የገነተ ጽጌ፣ ቸርችል፤ ፍልዉሃ እና ጥላሁን አባይ ቅርንጫፎችን ከተመለከቱ በኋላ እንደተናገሩት፥ ቅርንጫፎች እየሰጧቸው የሚገኙ የባንክ አግልግሎቶች ቀላል፣ ቀልጣፋና ለደንበኞች ምቾት መስጠት ላይ አተኩረው መሥራት ይገባቸዋል።
የባንክ አገልግሎት ሁልጊዜም እየዘመነና ድካምን እየቀነሰ መሄዱን ያስታወሱት አቶ ባጫ ጊና፥ ባንኩም በፍጥነት እየተለዋወጠ ከሚሄደው ዓለም ጋር አብሮ የሚራመድ አገልግሎት ማቅረብ ይገባል። ለዚህም ባንኩ ለቅርንጫፎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለደንበኞቹ የሚመጥን አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ጎን ለጎን በቅርንጫፎች እየተሰጡ የሚገኙ አገልግሎቶችን በአካል ተዘዋውሮ ምልከታ በማድረግና አስፈላጊውን የቁሳቁስና የሰው ኃይል በማሟላትና ስልጠና በመስጠት ክፍተቶችን መሸፈንና አገልግሎቶቹ በጥራት እንዲሰጡ የሚደረገው ጥረት በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ተጠናክሮ እንደሚሠራ ከጉብኝታቸው በኋላ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአንድ ወር የሚቆይ “የአገልግሎት ጥራት መሻሻል እናመጣለን” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚገኘው ንቅናቄ ያለበትን ሁኔታ የአመራር ቡድኑ የተመለከተ ሲሆን፥ ከደንበኞች ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት እንደተቻለው ባንኩ አገልግሎቶቹን ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በመስጠት የሚታወቅ በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጥራት መጓደሎችን በትኩረት ማስተካከል እንደሚገባው ለአመራር ቡድኑ ጠቁመዋል።
ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በመመልከት ክፍተት በታየባቸው ቅርንጫፎች ፈጣን ማስተካከያ እንዲያደርጉ አቅጣጫ በመስጠት ነው የዕለቱን ምልከታቸውን ያጠናቀቁት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን ከ1,560 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎች፣ ከ23.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ሲሆን፣ ከ3,000 በላይ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ ያለ አንጋፋና በሀገሪቱ ትልቁ ባንክ ነው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.