Home › Forums › Semonegna Stories › አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ
Tagged: አሸብር ባልቻ, አብርሃም በላይ, የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 9 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
February 22, 2020 at 6:02 pm #13672SemonegnaKeymaster
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር አብርሃም በላይ በጥር ወር 2012 ዓ.ም. የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ በምትካቸው አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል።
በጥር ወር 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ያገለገሉት ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ1973 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ አሸብር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በአምቦ አዲስ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀድሞ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፤ በአሁኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው 1995 ዓ.ም. ላይ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (Greenwich University) በዓለምአቀፍ ቢዝነስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከስዊዲን ሀገር ኬ. ቲ. ኤች ሮያል ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (KTH Royal Institute of Technology) በዘላቂ ኢነርጂ ምህንድስና ዘርፍ ተጨማሪ ኮርሶችን ወስደዋል።
አቶ አሸብር በሜካኒካል ምህንድስና ከተመረቁ በኋላ በበደሌ ቢራ ፋብሪካ ጀማሪ ሜካኒካል ኢንጂነር የሥራ መደብ ላይ ለ7 ወራት አገልግለዋል። ከነሐሴ 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቀጥረው በጊምቢ–መንዲ–አሶሳ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ሥራቸውን ጀምረዋል። በተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከጥር ወር 1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር 2003 ዓ.ም. ድረስ መሪ መካኒካል ኢንጂነር ሆነው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን በመቆጣጠር ተቋሙን አገልግለዋል።
ከግንቦት 2003 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ የገባ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ከጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ይህን ኃላፊነት እስከተቀበሉበት ቀን ድረስ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በተለያዩ የሥራ መደቦች በባለሙያነትና በኃላፊነት ለ16 ዓመታት አገልግለው ከየካቲት 09 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲመሩ በተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ተሹመዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድን እንዲመሩ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ዶ/ር አብርሃም እስካሁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደትክክለኛው መስመር እንዲመጣና እንዲፋጠን ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይም በኢፌዲሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ተይዘው የነበሩ ሥራዎች ልምድ ላላቸው ዓለም አቀፍ ተቋራጮች እንዲሰጥና ተቋራጮቹም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ጉልህ የአመራር ሚና ነበራቸው። የገናሌ ዳዋ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የካሳ ጥያቄ እልባት አግኝቶ ለምርቃት እንዲበቃም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ቢተገበሩ ወጪ ከማውጣት ባለፈ ውጤታማ የማይሆኑ ረዥም ዓመታት የወሰዱ ፕሮጀክቶች በህጋዊ መንገድ እንዲቋረጡ በማድረግ ተቋሙንና መንግስትን ከተጨማሪ ወጪ ማዳን ችለዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጤናማ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው በማድረግና በተቋሙ የአሰራር ስርዓቶችን በማሻሻል ተጨባጭ አምጥተዋል።
የተቋሙን የዕዳ ጫና በተመለከተ ተቋሙ የሚመለከተውን ብድር ብቻ እንዲሸከምና ሌሎች ብድሮች ግን ወደ ብድሩ ባለቤቶች እንዲተላለፉ የሚያስችል ቁርጠኛ አቋም በመያዝ የብድር ጫናው እንዲቀንስ አድርገዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል በማሰብ እና በተቋሙ ላከናወኑት ሥራ እውቅና ለመስጠት ተቋሙን በሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ዶ/ር አብርሃም ባሳዩት ውጤት በተቋሙ አመራር እና ሰራተኞች ዘንድ ተወዳጅ የነበሩና የለውጥ መሪ ተምሳሌት ተደርገው የሚወሰዱ ነበር። የተቋሙ አመራርና ሠራተኞችም ዶ/ር አብርሃም በሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት ዳግም ወደተቋሙ በመምጣታቸው ደስታቸውን ገልፀዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.