አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ወቅቱን ያገናዘበ የቴክኖሎጂ ስልጠና ማዕከል ለማስገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም. በተቋሙ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራርሟል።
ሁለቱን ተቋማት ወክለው የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራ ተሊላና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር ነገደ አባተ ናቸው።
የቴክኖሎጂ ስልጠና ማዕከሉ ግንባታ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን፥ በምዕራፍ አንድ የግንባታ ጥናትና የዲዛይን ሥራዎች፣ በምዕራፍ ሁለት የህንጻ ግንባታ ቁጥጥር እና የውል አስተዳደር ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል።
የስልጠና ማዕከሉ ግንባታ የሚከናወነው አዲስ አበባ ኮተቤ በሚገኘው 16.9 ሄክታር መሬት ላይ ነው። ግንባታው የሚከናወነው የከተማውን ሕግና የህንጻ ግንባታ ስታንዳርድ እንዲሁም ማስተር ፕላን መሠረት በማድረግ መሆኑንም በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።
የማዕከሉ ሕንጻ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ በአማካሪ ማሀንዲሱ ጨረታ ከወጣ በኋላ የሚወሰን ሲሆን፥ የማዕከሉ ማስተር ፕላን ለማዘጋጀት፣ ለዲዛይንና ኮንትራት አሰተዳደር ሥራዎች ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረግበታል።
የቴክኖሎጂ ማዕከሉ የመማሪያ ክፍል፣ የአስተዳደር ህንጻ፣ ቤተ-መፅሐፍት፣ የምርምርና የልህቀት ማዕከል፣ መኝታ ቤቶች፣ ልዩ ልዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችና የማሰራጫ (distribution) ሥራዎች ሠርቶ ማሳያ የሚኖረው ይሆናል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራ ተሊላ በፌርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገነባው የስልጠና ማዕከል ተቋሙ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በቴክኖሎጂ በመደገፍ የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና አስተማማኝ ለማድረግ፣ የአቅም ውስንነቶችንና የመረጃ ከፍተቶች ለመሙላት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም የኦፕሬሽንና የቢዝነስ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ የከፍተኛ ቮልቴጅ እቃዎችን ጥራት ለመፈተሽና ለማረጋገጥ፣ የማሰራጫ (distribution) መስመሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስካዳ ሲስተም (SCADA system) ተግባራዊ ለማድረግም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጅነር ነገደ አባተ በበኩላቸው የስልጠና ማዕከሉ አቅም ያላቸው ባለሞያዎችን ለመፍጠር የሚያስችልና ለሌሎች ተቋማትም ማሳያ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የስልጠና ማዕከሉ ግንባታ የጥናትና የዲዛይን ሥራዎችን ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቁ በኋላ የሚጀመር መሆኑን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ተጠቁሟል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ