Home › Forums › Semonegna Stories › የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በጠራው ስብሰባ ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ
Tagged: Wolaittatto Doona, ወላይትኛ, የወላይታ ዞን ምክር ቤት
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 4 years, 6 months ago by Anonymous.
-
AuthorPosts
-
June 23, 2020 at 2:48 am #14894AnonymousInactive
የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በጠራው ስብሰባ ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ
የወላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ-መንግሥት መሠረት አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ ይታወቃል። ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ወላይታ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ቢደነግግም የክልሉ ምክር ቤት የወላይታን ክልል የመመሥረት ጥያቄን ለምክር ቤት እንደ አጀንዳ ላለማቅረብ በማሰብ መደበኛ ስብሰባዎችን በተደጋጋሚ ሆን ብሎ እየዘለለ ቆይቷል።
ከዚህም ባሻገር የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ባካሄዳቸዉ አስቸኳይ ጉባዔዎች የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ለጉባዔው እንዳይቀርብ የተደረገ ሲሆን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በምክር ቤቱ አጀንዳ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ታፍነዉ ዕድል እንዳይሰጣቸዉ ተደርገዋል።
ይህንን ኢፍትሐዊ አሠራር መነሻ በማድረግ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አስቸኳይ ጉባኤ የጠራ ሲሆን፥ በዚህ አስቸኳይ ጉባዔ በዋናነት የዞኑ መስተደድር የሕዝቡን ክልል የመመሥረት ጥያቄን የመራበት ሂደት በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን፥ እስካሁን ያለው ሂደት አመርቂ መሆኑንም ገምግሟል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በስፋትና በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተለዉን ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፤
- የወላይታ ሕዝብ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47 (3) መሠረት የጠየቀዉ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የሚመሠረተዉ ክልል ስያሜው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የሥራ ቋንቋ ወላይትኛ (Wolaittatto Doona)፣ የክልሉ ርዕሰ-ከተማ ‹‹ወላይታ ሶዶ›› ይሆናል። ስለሆነም መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ለሆነ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ–መንግሥትን በተከተለ መንገድ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የወላይታ ብሔር ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።በተጨማሪም ይሄ ጥያቄ በጊዜ ባለመመለሱ የተነሳ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰ፣ የዞኑ መንግሥት ሙሉ ጊዜውን በልማት ሥራ እንዳያውል እንቅፋት እየሆነ የሚገኝ በመሆኑ ሂደቱም ወደ ፀጥታ ችግር ሳይሸጋገር የፈደራል መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ እንዲሰጥ ምክርቤቱ ጠይቋል።
- የወላይታ ብሔርን ወክለዉ በክልል ምክር ቤት ሲሳተፉ የነበሩ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በቀን ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደዉ 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ላለመሳተፍ ራሳቸዉን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸዉ ለሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነዉ። ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት ለወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ነዉ። ይህ የወላይታ ብሔር ተወካዮች ውሣኔ ለወላይታ ብሔር ያላቸዉን ክብር የሚያሳይ ስለሆነ ምክር ቤቱ በአድናቆት ተመልክቷል። ነገር ግን እነዚህን ተወካዮች የክልሉ አስተዳደርና የክልሉ ምክር ቤት ጠርተዉ ማወያየት ሲገባዉ እስካሁን ድረስ ዝም ማለቱ መላዉን የወላይታ ሕዝብ አለማክበሩን ያሳያል። የሕዝብ ውክልና የያዘ አካል ለክልሉ ምክር ቤት ያለዉን ቅሬታ ለማሳየት መልቀቂያ ቢያስገባ የዚህን ሕዝብ ተወካዮች ጠርቶ አለማወያየትና ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን እንገነዘባለን። የወላይታ ሕዝብ በሀገሪቱ ለመጣዉ ለዉጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ ታሪክ ያለዉ ሕዝብ ነዉ። ስለዚህም የፌዴራል መንግሥት እነዚህን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮችን ጠርቶ እንዲያነጋግር የዞኑ ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።
- የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚወስናቸው ወላይታን የሚመለከት ማንኛውም ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በወላይታ ዞን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ወስኗል። በተጨማሪም በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚወስኑ የወላይታ ሕዝብ ጥቅም የሚጎዱ ማነኛውም ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክር ቤቱ ወስኗል።
- የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅር የሚመሩ አካላት ላይ እምነት ስሌለንና ገለልተኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፓስት (Command Post) የሚመራ በመሆኑ የወላይታ ዞን ፀጥታ ሥራ በሕዝቡ እና በዞኑ ፀጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መፈፀም እንዳለበት እና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከፈደራል ፀጥታ መዋቅር በትብብር መሠራት እንዳለበትም ተወስኗል።
- ወደፊት የሚመሠረተው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፓለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ ሰክራቴሪያት ፅ/ቤት እንዲቋቋም ተወስኗል። በተጨማሪም የዞኑ መንግሥት እንደየአስፈላጊነቱ ለወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሂደቱን በበላይነት እንዲመራም ተወስኗል።
- ቀጣይ ሕዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ተወስኗል።
- የወላይታና አጎራባች ሕዝቦች ትስስር ለዘመናት የቆየና በቀጣይ አብሮ የሚኖርና የሕዝቦች ትስስር ከመዋቅር በላይ በመሆኑ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ምክር ቤት ወስኗል።
ለመላዉ የወላይታ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት ሕገ–መንግሥታዊ መብት በሚመለከተው ፌዴራል መንግሥት አካል ለጥያቄዉ ተገቢ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ እንደተለመደው ሁሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
“የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና ዓለማቀፍ ሕግ ያጎናጸፈዉ የወላይታ ሕዝብ ክልል የመመሥረት መብት ጥያቄ በሰላማዊ ሕዝብ ትግል እውን ይሆናል!”
ሰላም ለሀገራችን
የወላይታ ዞን ምክር ቤት
ወላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. -
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.