Home › Forums › Semonegna Stories › የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ባለስልጣናት በተገኙበት በይፋ ተመረቀ
Tagged: Worabe University, ሂሩት ወልደማርያም, አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ, ወራቤ ዩኒቨርሲቲ, ጎንደር የኒቨርሲቲ
- This topic has 0 replies, 1 voice, and was last updated 5 years, 12 months ago by Semonegna.
-
AuthorPosts
-
November 30, 2018 at 8:07 pm #8749SemonegnaKeymaster
ወራቤ (ሰሞነኛ)–በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሚገኘው የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት በተገኙበት ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ካስተላለፉት መልዕክት ስለ ክልላዊነትና ዓለም አቀፋዊነት (localization and internationalization) የተናገሩት የሚገኝበት ሲሆን በንጽጽር መልክ ባስቀመጡት በዚህ ንግግራቸው ዓለማቀፋዊነት አጉልተው በማሳየት የሚከተለውን ብለዋል።
ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የዩኒቨርሲቲ መሰረታዊና ልዩ መለያ ባህሪዎች ናቸዉ። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ማኅበረሰቦች የብዝሃነት ባህሪን የሚገልጹ ሲሆን፤ ይህም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በአመራሩ እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አከባቢያዊ እና ህብረብሄራዊ አመጣጥ ይገለጻል።
ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ተቋማት እንደመሆናቸዉ መጠን ተማሪዎች በየአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንዲማሩ፣ መምህራንም በአካባቢያቸው ባለው ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተቀጥረው እንዲያስተምሩ፣ አመራሩም በተወለዱበት አከባቢ የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ ብቻ እንድያስተዳድሩ የሚለው አስተሳሰብ ከዩኒቨርሲቲ ብዝሃነትና ዓለም አቀፋዊነት የማስተናገድ ባህሪ የወጣ ስለሚሆን የዩኒቨርሲቲዎቻችንን ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ነዉ።
ዓለም አቀፍ ቶሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩበት አንዱና ዋነኛው መስፈርት፣ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍል ለሚመጡ ተማሪዎችና ሠራተኞች አቃፊ በመሆናቸውና ዓለም አቀፋዊነትን በማስተናገዳቸው ነው። ዩኒቨርሲቲዎች አለማቀፋዊነት ባህሪ እንጂ አካባቢያዊ ዉስንነት እንደማይመጥናቸዉ ያሳያል።
ስለዚህ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና አሠራር በተቃራኒ አቅጣጫ መሄድ የለብንም! የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ከብሄራዊ አስተሳሰቦች አልፎ ዓለም አቀፋዊነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎቻችንን በአካባቢያዊነትና በባህል በመከፋፈል፣ ባህላዊና ክልላዊ ማድረግ ወይም መከፋፈል አያስፈልግም።
በሌላ የከፍተኛ ትምህርት እንቅስቃሴ ዜና፥ የጎንደር የኒቨርሲቲ ለሴት መምህራንና ሠራተኞች በወሊድ ወቅት በመደበኛነት የሚፈቀድላቸውን የወሊድ ፈቃድ አጠናቀው ወደ ሥራ በሚመለሱበት ጊዜ ህፃናትን በሥራ ቦታ የማቆያና የመንከባከቢያ ማዕከል ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ክብርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ባስተላለፉት መልዕክት “የህፃናት ማቆያ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መጀመሩ ትልቅ ሥራ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴቶችን ተሳትፎና ስኬታማነት ከማረጋገጥ አኳያ በጣም ትልቅ ሚና መኖሩን ገልፀው፥ ሴት መምህራን በሥራ ገበታቸው ላይ ቤት ትተው የመጡትን ህፃን በማሰብ በተከፈለ ልብ እንዳይሰማሩና ከወንድ አቻቸው ጋር ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ይህ የህፃት ማቆያ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።
የዚህ ዓይነቱ የህፃናት ማቆያ ማዕከል በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢስፋፋ ሴቶች መምህራን በጥናትና ምርምር ሥራቸው ላይ አትኩረው እንዲሠሩ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
-
AuthorPosts
- You must be logged in to reply to this topic.